የሀገራዊ ምክክር ዋጋ ስንት ነው?
ግንቦት 3/2018 ዓ.ም
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሃሳብ ልዩነቶች ምክንያት የገባችባቸውን አስከፊ ግጭቶች ስንመለከት እንደ ሀገር የደረሰብን ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ማህበራዊ ኪሳራዎች እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ በዘመናት ለተፈጠሩ ቅራኔዎች እና ቁርሾዎች መፍትሔ ለማፈላለግ የተሄደባቸው የተለያዩ የግጭት መፍቻ መንገዶችንም ስንመለከት ለተለያዩ የሙዓለ-ነዋይ ወጪዎች እንደዳረጉን ተመልክተናል፡፡
ለመሆኑ ከሌሎች የግጭት መፍቻ መንገዶች ጋር በትይዩ ሀገራዊ ምክክር ምን ያህል ወጪ ሊያስወጣ እንደሚችል ገምተው ያውቃሉ? የሀገራዊ ምክክር የመጨረሻው ግብ የሰው ልጆችን እልቂት አስቀርቶ መግባባትን ዕውን ማድረግ በመሆኑና ይህም በገንዘብ የማይተመን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሂደቱ የተለያዩ ወጪዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ይታወቃል፡፡
በእርግጥ ሀገራዊ ምክክር ከበርካታ የግጭት መፍቻ መንገዶች ጋር ሲነፃፀር በተለያዩ ረገዶች አነስተኛ ሊባል የሚችል ወጪን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሂደቱን ለማከናወን መሰረታዊ የሎጂስቲክስ፣ የጊዜ እና ተያያዥ ጉዳዮች በራሳቸው በሙዓለ-ነዋይነት የሚያዙ ቢሆንም ሀገራዊ ምክክር በዋነኛነት የሚጠይቃቸው ወጪዎች ተፈጥሮ ግን ከሌሎች የግጭት መፍቻ መንገዶች ይለያል፡፡ እነዚህ ወጪዎች የተመካካሪዎችን ሥነ-ልቦና ማዕከል ያደረጉ ሲሆን በአመዛኙ ሰብዓዊነት ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ የሚከተሉት ሃሳቦች ሀገራዊ ምክክር ከሌሎች የግጭት መፍቻ መንገዶች ጋር ሲነፃፀር የሚጠይቀውን ዋጋ ከብዙው በጥቂቱ ያብራራሉ፡፡
1. ስምምነት ላይ ለመድረስ መስዋዕትነትን መክፈል
በአንዳንድ ሀገራት በተደረጉ የምክክር ሂደቶች ያለፉ የፖለቲካ ኃይሎች መግባባትን ዋነኛ ዓላማቸው አድርገው ወደ ሂደቱ በመግባታቸው ሁሉም በየበኩላቸው እጅግ ከባድ ሊባሉ የሚችሉ የመርህ እና የአቋም ማስተካከያዎችን አድርገዋል፡፡ ይህም ከራስ በላይ ሀገርን በማስቀደም የጊዜ፣ የዕውቀት፣ የጉልበት፣ የሥነ-ልቦና እና የስሜት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆንን እንደሚጠይቅ ያስገነዝበናል፡፡
2. ከፉክክር መንፈስ ይልቅ በሰብዓዊነት የሌሎችን ችግር ለማድመጥ መዘጋጀት
ሀገራዊ ምክክር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እርስ በእርሳቸው በሰብዓዊነት እና በርህራሄ አንዱ የሌላውን ችግር እንዲያዳምጡ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ከፉክክር እና ክርክር መንፈስ ይልቅ ሌላውን በእውነት ለመረዳት በር ከፋች ነው፡፡ ይህም በተለያየ ደረጃ ሊገለፁ የሚችሉ የሞራል እና የሥነ-ልቦና ጥንካሬ እንደሚጠይቅ መመልከት ይቻላል፡፡
3. ለዘመናት የያዝናቸውን አቋሞች ለመቀየር መፍቀድ
በሀገራዊ ምክክር ውስጥ ተሳትፎን ስናደርግ አንዳችን ሌላችንን በአግባቡ ሳንረዳ የተለያዩ አስተሳሰቦችን እና የገነገኑ አመለካከቶችን አዳብረን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ ሂደት ሁሉም ባለድርሻ አካል የራሱን ሰብዓዊ እውነታ ይዞ የሚቀርብበት በመሆኑ ከአንዳንድ አቋሞች ጀርባ ያሉ ፍላጎቶችን እና እውነታዎችን እንድንገነዘብ ምክንያት ይሆነናል፡፡ ይህም ተመካካረዎች አንዳንድ እውነታዎችን በሚገነዘቡበት ወቅት አቋሞቻቸውን እንዲለውጡ እና የእኔ ብለው የያዙትን ‘እውነታ’ ዳግም እንዲያጤኑት ያደርጋል፡፡
4. ትዕግስት እና ፅናትን ማጎልበት
የሀገራዊ ምክክር ሂደት የአንድ ቀን ወይም የአንድ ወቅት ክስተት እንደማይሆን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሂደቱ ባልተግባባንባቸው ጉዳዮች ላይ ምንአልባትም ለአመታት ለመነጋገር ፍቃደኝነታችን የሚጠይቅ እንደሚሆን ማወቁ ጠቃሚ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ የማንግባባቸው ጉዳዮች መኖራቸው ለግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ ተስማምተን በምክክር በይደር እያቆየን ለመፍታት መወሰን በራሱ የሥነ-ልቦና፣ የስሜት እና የጊዜ መስዋዕትነትን ያስከፍላል፡፡
በመሆኑም ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ የምንኖር ሕዝቦች ራሳችንን በታማኝነት ፈትሸን በሃሳብ ልዮነቶች ላይ ለመነጋገር መፍቀዳችንን የሚጠይቅ ሂደት እንደመሆኑ በቁጥር የማይተመኑ ረቂቅ የሆኑ ዋጋዎች ይኖሩታል፡፡ ይህም ውድ የሆነውን የሰው ልጆችን ህይወት ከሚቀጥፈው ጦርነት ጋር ሲነፃፀር ምክክር አዋጭ የመግባቢያ መንገድ እንደሆነ መገንዘብ ያስችላል፡፡
ሀገራዊ ምክክር ለሀገራዊ መግባባት!





