ምክንያታዊነት በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት እንዴት እየተቃኘ ነው?
ግንቦት 10/2018 ዓ.ም
ምክንያታዊነት በአንድ ሀገር ውስጥ ለሚከናወን የሰላም ግንባታ እና የምክክር ሂደት ዋነኛውን ሚና ይጫወታል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተቋቋመበት የመመስረቻ አዋጅ ላይ ምክንያታዊነት ከሀገራዊ ምክክሩ መርሆዎች አንዱ ተደርጎ መደንገጉ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ፅንሰ-ሀሳቡ በምክክር ሂደት ውስጥ በምን መንገድ እየተተገበረ እንዳለ ማወቁ አስፈላጊ ነው፡፡
በሀገራዊ ምክክር ዓውድ ውስጥ ምክንያታዊነት ከስሜታዊነት፣ ከጥላቻ እና ከሃሳብ ግትርነት የፀዳ በአንፃሩ አመክንዮን እና ማስረጃን መሰረት ያደረገ ውይይቶችን ለማድረግ እና ውሳኔዎችን ለማሳለፍ የሚያግዝ ቁልፍ የሥነ-ምግባር መርህ ነው፡፡ ይህም ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የጋራ መፍትሔን ለመፈለግ የሚያደርጉትን በጎ ጥረት ያጠናክራል፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ ምክንያታዊነት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ እንዴት ተፈፃሚ እንደሚሆን የሚከተሉት ሀሳቦች ያብራራሉ፡፡
1. አመክንዮን እና ማስረጃን መሰረት በማድረግ
በዚህ ሂደት ዜጎች እና ባለድርሻ አካላት ከስሜታዊነት እና ጥላቻ በፀዳ አኳኋን በውይይቶች ላይ ተሳትፎን ማድረግ ያደርጋሉ፡፡ ይህም የምክክሩ ዓውድ ሰላማዊ እንዲሆን የማድረግ አቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡
2. ገለልተኝነትን እና ፍትአዊነትን መሰረት በማድረግ
ምክንያታዊ የሆነ የሀገራዊ ምክክር ሂደት ሚዛናዊ የሆኑ ውይይቶች እንዲደረጉ ከማገዙም በላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድምፆቻቸው በእኩልነት እንዲሰሙ በር ከፋች ነው፡፡
3. በሰው ልጆች እኩልነት ማመንን በማበረታታት
በሀገራችን የሚደረጉ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች የሰው ልጆች በጋራ ችግሮቻቸው ላይ የሚወያዮባቸው እንደመሆናቸው መጠን የሰው ልጀችን እኩልነት እና ተፈጥሯዊ ማንነት በማክበር እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡





