የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች

በኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በግልጽ እንደተመላከተው በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ነጻና ገለልተኛ በሆነ ተቋም መመራት ስላላበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ በዚሁ አዋጅ ኮሚሽኑ ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነትና ተጽእኖ ነጻ ሆኖ ስራውን ማከናወን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ይህ ለኮሚሽኑ ነጻና ገለልተኝነት የህግ መሠረት ያለው መሆኑ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ በአዋጁ ዝርዝር ጉዳዮችም ኮሚሽኑ የሚከናውናቸውን ተግባራት በገለልተኝነትና በነጻነት ለማከናወን የሚያስችል አዋጅ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

አዋጅ 1265/2004 ስራዎች የሚከናወኑባቸው መርሆዎችን ከማስቀመጥ ባለፍ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ አለመገባቱም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ የምክክሩን ተሰታፊዎችንም ሆነ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች ኮሚሽኑ መርሆዎችን መሠረት በማድረግ በራሱ እንዲወስን ሰፊ እድል የሰጡ ናቸው፡፡ የኮሚሽኑን ስራ በበላይነት የሚመራው ምክር ቤት አባላት የሆኑት ኮሚሽነሮች አመራረጥና አሰያየምም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ ኮሚሽኑ ባለው አሰራርም የየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ነው ያለው፡፡

አንዳንድ ወገኖች ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መሆኑን እንዲሁም በጀት ከመንግስት የሚመደብለት በመሆኑ ነጻና ገለልተኛ ነው ብለው ለመቀበል እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ግን ሚዛን የሚደፋ አይደለም፡፡ በሀገራችን ነበራዊ ሁኔታ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤ መሆኑ አንጻራዊ ገለልተኝነቱን የሚያስጠብቅለት የተሻለው አማራጭ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች ሀገራት ተጠሪነታቸው ለሀገሪቱ ከፍተኛ አካል ማለትም ለህግ አውጭው ሆነው ስራቸውን በገለልተኝነትና በነጻነት አከናውነው ውጤታማ የሆኑ ተቋማት መኖራቸውን ማጤኑም ጠቃሚ ነው፡፡ በጀትን በተመለከተም መንግስት ለኮሚሽኑ የሚበጅተው በታክስ፣ በእርዳታ ወይም በበድር ከሚያገኘው ጥሪት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ነው፡፡ በመሆኑም ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን ህዝብ ሀብት ተጠቅሞ ለህዝቡ መስራቱ ገለልተኝነትና ነጻነቱን ይበልጥ የሚያጠናክርለትና በከፍተኛ ሀላፊነት እንዲሰራ የሚደርገው ነው፡፡ ከቀደሙ ተሞክሮዎች ለመገንዘብ እንደሚቻለውም ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ መሆን የሚችለው በሀገር ባለቤትነት ሲያዝ ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመሠረታዊና ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ አሳታፊና አካታች ምክክር እንዲካሄድ በማድረግ መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች በሚመለከታቸው አካላት ተፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ የምክረ ሀሳብና የአፈጻጸም ዕቅድ አዘጋጅቶ ማቅረብ እንዲሁም ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዳለበት በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አኳያ የሚመለከታቸው አካላት ምክረ ሀሳቦቹን ለመፈጸም ተገቢውን ጥረት ባያደርጉ ወይም ምክረ ሀሳቦቹን ለመቀበል አሻፈረኝ ቢሉ የኮሚሽኑ የአስገዳጅነት አቅም ምን ድረስ ነው? የሚል ጥያቄ ተደጋግሞ ይቀርባል፡፡  

በእርግጥ ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳቦቹ እንዲተገበሩ ማድረግ የሚያስቸለው ሁነኛ አቅሙ የህዝብና የባለድርሻ አካላት አጋርነት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሂደቱን አሳታፊ፣ አካታችና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ የሚሆነው፡፡

በሌላም በኩል በመፈጸም ረገድ ዋነኛ ተዋናይ የሚሆነው መንግስት ፖለቲካዊ ፍላጎቱንና ቁርጠኝነቱን በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ እየገለጸም ነው ያለው፡፡ ምንም እንኳ የሀገራዊ ምክክር ጥያቄው በተለያየ ጊዜ በተለያዩ ወገኖች ሲቀርብ የቆየ ቢሆንም አሁን በሥልጣን ላይ ባለው መንግስት ፖለቲካዊ ፍቃደኝቱ ተገኝቶ ሂደቱን የሚመራ ኮሚሽን በአዋጅ ማቋቋም ተችሏል፡፡ በቀጣይ የሚያስፈልገው ኮሚሽኑ ሂደቱን በገለልተኝትና በነጻነት እንዲመራ ጣልቃ ባለመግባት፣ የሚያስፈልገውን ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ምክረ ሀሳቦችን ተቀብሎ ተግበራዊ በማድረግ የሚገለጽ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይ ግጭትን በማስቆምና እንዳይባባስ በማድረግ ረገድ ውስንነቶች የሚታዩ ቢሆኑም የጎሉ ችግሮች አልተስተዋሉም፡፡ በዚህ ልክ ህዝብና ባለድርሻ አካላት ተመካክረው የተግባቡበትን ጉዳይ ለሕዝብ የማሳወቅ መብት ለኮሚሽኑ የተሰጠው በመሆኑ ፈጻሚው አካል የማይፈጽምበት ሁኔታ ቢያጋጥም እንኳ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ከተጠያቂነትና ከታሪክ ተወቃሽነት የሚያፈገፍግበት እድል ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡

በተወሰኑ ወገኖች ተደጋሞ የሚነሳና መሠረታዊ የአተያይ ጉድለት ያለበት አመለካከት ነው፡፡

1ኛ- ምክክሩ የሚካሄደው እጅግ መሰረታዊ በሆኑና አለመግባባት ወይም የሀሳብ ልዩነቶች በሚታይባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ ሀገራዊ ያውም እጅግ መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮች ሆነው በተለያየ ማህበረሰብ የሚወከለውን ሕዝብ አይመለከተውም ማለት የሚቻልበት አግባብ የለም፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አለመግባባቶች በመኖራቸው ዋነኛ ተጎጂ የሆነውና በህይወት የመኖር፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና በሀገሩ ሀብት ንብረት የማፈፍራት፣ መሰረታዊ የትምህርትና የጤና አገልግሎት የማግኘት መብቶቹ ጥያቄ ውስጥ የወደቁበት ሕዝብ በመሆኑ ከዚህ አዙሪት ውስጥ ለመውጣት ህዝቡ ባለድርሻ መሆን አይገባውም የሚል መከራከሪያ ሚዛን አይደፋም፡፡

2ኛ- ህብረተሰቡን በምክክሩ ሂደት ማሳተፍ ለምን ያስፈልጋል የሚሉ ወገኖች በምክንያትነት የሚያነሱት ሌላው ጉዳይ ያልተግባባው ወይም የተጣላው ህዝቡ ሳይሆን ፖለቲከኛውና ሊሂቃኑ በመሆኑ የኮሚሽኑ አካሄድ ዋነኛ ባለጉዳዮች ላይ አላተኮረም የሚል ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የሀሳብ ልዩነቶች ወይም አለመግባባቶች በሂደት ስር እየሰደዱ ወደ ማህበረሱም እየሰረጹ መሆናቸውን ማጤኑ ተገቢ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማህበረሰቡ የሀሳብ ልዩነት ወይም አለመግባት ምንጭ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ልዩነት የለውም የሚባል ከሆነም በምክክሩ ሁነኛ ተሳታፊ ሆኖ በቱርጅማን በወይም እርሱን በማይመስሉ ተወካዮች ሳይሆን በቀጥታ በራሱ ተወካዮች ሀሳቡን መግልጹ በራሱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

3ኛ- በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሊሂቃንና ፖለቲከኞችን የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ወኪል አድርጎ መውሰድ የሚቻልበት አግባብም የለም፡፡ በርግጥ የሀሳብ መሪዎችና ፖለቲከኞች ሀሳቦቻቸውን ወደ አደባባይ ሲያመጡ ብዙውን ጊዜ ለሚወክሉት ህዝብ ጥቅም አድርገው ማቅረባቸው የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም በተፈጥሯዊ ባህርያቸው ምክንያት ወይም በሀሳብ መሪዎችና በፖለቲከኞች ዘንድ ባለ የቅቡልነት ችግሮች ምክንያት ሁሉም ወገኖች በነዚህ አካላት መወከል ይችላሉ ወደሚል ድምዳሜ መድረስም አዳጋች ነው፡፡

ከዚህ ይልቅ የህዝቡን ጉዳይ እኛ እናውቅለታለን የሚሉ ወገኖችም እይታቸውን መቀየር፣ ህዝቡም እነሱ ያውቁልኛል ከሚል ጥቅል ድምዳሜ መውጣትና በተሰጠው እድል ሀሳቡንና ድምጹን በማሰማት ታሪካዊ ዕድሉን ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ይህንንም የማድረግ አቅምና ፍላጎት አለው፡፡

3ኛ- የጥያቄው መነሻ ሀሳብ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበትን አዋጅ በአግባቡ ባለመረዳት ወይም ሆን ብሎ ሸፍኖ የማለፍ ችግር ያለበትም ይመስላል፡፡ኮሚሽኑ በአዋጅ የተቋቋመና ስራዎቹን ህግን መሠረት አድርጎ የሚሰራ ነው፡፡ በአዋጁ የሀሳብ ልዩነቶቹ ወይም አለመግባባቶች የሚታዩት በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካና እና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ከፖለቲካና ከሀሳብ መሪዎች በተጨማሪ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተብለው የተገለጹትን በአግባቡ ትርጉም መስጠትና ማሳተፍ የተሳታዎች መብት ከመሆኑ ባሻገር የኮሚሽኑም ህጋዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚሁ አዋጅ መሠረት የአጀንዳ ሀሳቦች የሚሰባሰቡትም ሆነ ምክክሩ የሚደረገው እነዚህኑ አካላት በማሳተፍ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም ፖለቲከኞች ተሳትፎ ላይ ጥያቄ ሲነሳ አይሰተዋልም፡፡ የህብረተሰቡ ተሳትፎን በተመለከተም በዚሁ ደረጃ መመልከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

በምክክር ሂደት ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱና ባለድርሻ ከሆኑ አካላት መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በሂደት ላይ ያለውን ምክክር ከጅምሩ ለመቀበል ፍላጎት ያልነበራቸው በርካታ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ በሂደት ባነሷቸው ጥቄዎች ላይ ውይይቶችን በማድረግ ለመግባባት በተደረጉ ጥረቶች ሂደቱን በመደገፍ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ካሉም ለማስተካከል በመተማመን በርካታ ፓርቲዎች በሂደቱ እየተሳተፉ ናቸው፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ሁኔታውን ለማጤን ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ወይም ለመቀበል እንደሚቸገሩ በመግለጽ በሂደቱ እየተሳተፉ አለመሆናቸው ይታወቃል፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች ላለመሳተፋቸው በምክንያትነት ሲጠቅሱ ከሚደመጥቧቸው ጉዳዮች መካከል ኮሚሽኑ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ለመስራት የሚችልበት ዕድል ጠባብ ነው በተለይ የገዢው ፓርቲ ጫና አለበት፣ በሀገሪቱ ግጭቶች እየተካሄዱ ባለበት ሁኔታ አስቀድሞ ግጭቶቹ ሳይቆሙ ምክክር ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ የለም እንዲሁም በምክክር መግባባት ላይ የሚደረስባቸውን ጉዳዮች በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም መንግስት ቁርጠኝነቱ ላይኖረው ይችላል፣ ኮሚሽኑም የተሟላ የማስፈጸም ስልጣን አልተሰጠውም የሚሉና መሰል ጉዳዮች ናቸው፡፡

በመሠረቱ እነዚህ ከጥርጣሬ ወይም ከጥንቃቄ የሚመነጩ ጥያቄዎች ሂደቱን ባልተቃለቀሉ ብቻ ሳይሆን ተቀብለው እየሰሩ ያሉትም የሚያነሷቸው ናቸው፡፡ ከፖለቲካው ውጭ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም ሲነሱ ይሰተዋለል፡፡ ለነዚህ ጉዳዮች ትክክለኛውን መልስ ማግኘት የሚቻለው ግን በሂደት ነው፡፡ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ለመወጣት በሚያደርገው ያለሳለሰ ጥረት ላይ የሚወሰን እንጂ ከዳር ሆኖ በመመልከት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ ፓርቲዎችም ለሚያነሷቸው ስጋቶች ተጨባጭ ማሳያዎችን ለማቅረብም ሲቸገሩ ይስተዋላሉ፡፡

የኢትዮጵ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉም ፓርቲዎች በሂደቱ እንዲሳተፉ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ፓርቲዎች እንደ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሁሉ በአጀንዳ ሀሳቦች የማሰባሰብና የምክክር ሂደት ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ከመሆናቸው በተጨማሪም አሉን የሚሏቸውን የአጀንዳ ሀሳቦች በቀጥታ ለኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ፣ ሁሉም እኩል እድል ተሰጥቷቸው ተሳተፊ እንዲሆኑ፣ ከህብረተሰቡ ተሳተፊዎች በሚለዩበት ወቅት እንደ አንድ ተባባሪ አካል እንዲሰሩ እንዲሁም በኮሚሽኑ የአማካሪ ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው የድርሻቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር እየሰራ ነው፡፡ በሂደቱ እያልተሳተፉ ያሉ ፓርቲዎችም እንዲሳተፉ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እደረገ ነው፡፡

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር ከሚመራባቸው መርሆዎች አንዱ አካታችነትና አሳታፊነት ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት በሀገሩ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ሁሉም ባለድርሻ አካል  እንዲካተትና እንዲሳተፍ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ይህም የህግ የበላይነትን ባከበረ መልኩ ነው የሚካሄደው፡፡ በዚህ አግባብ  በመርህ ደረጃ በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖችም የሂደቱ ተሳተፊ መሆናቸው አስፈላጊ እንደሆነ ኮሚሽኑ ያምናል፡፡ እነዚህ ወገኖች ወደ ግጭት እንዲገቡ የተገፉባቸው የልዩነነት አጀንዳዎች አሏቸው ብሎ ኮሚሽኑ ያምናል፡፡ ነገር ግን ወደ ምክክሩ ሲመጣ የሀይል አማራጮች ዝግ ተደርገው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡  የሀይል አማራጭንም ምክክርንም ጎን ለጎን ማስኬድ ውጤታማ ያደርጋል ተብሎ አይታመንም፡፡ በመሆኑም መንግስትን ጨምሮ በግጭት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች ግጭቶቻቸውን በተለያዩ አማራጮች ፈትተው አጀንዳዎቻቸውን ወደ ምክክሩ ጠረጴዛ በማምጣት እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ ከተላዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስራውን ለማከናወን እንዳስፈላጊነቱ ሊራዘም የሚችል የ3 አመት ጊዜ በአዋጅ እንደተሰጠው ይታወቃል፡፡ ኮሚሽኑም ይህንኑ መሠረት በማድረግ የ3 አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ተግባራትን ለማካናወን አስቻይና ፈታኝ ሁኔታዎችን በመተንተን ማቀድ አንድ ነገር ሆኖ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች መፈጠርና የፈታኝ ሁኔታዎች እየተባባሱ መሄድ ስራን በአግባቡ ማከናወንን እጅግ አስቸጋሪ ያደርጉታል፡፡

ኮሚሽኑ ስራ የጀመረበት የመጀመሪያው አመት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጦርነት የተካሄደበት መሆኑ ይታዋቃል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የምክክሩን ሂደት በተሟላ መልኩ ለማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይህም ሆኖ ሁኔታዎች እስኪሻሻሉ ድረስ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን በተለይ በአማራና በኦሮሚያ የተወሰኑ ዞኖች ያሉ የጸጥታ ችግሮች አሳሳቢ እንደሆኑ ቀጥለዋል፡፡

በነዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በዕቅድ መሠረት ስራውን ለማከናወን የተቸገረው ኮሚሽኑ የማካካሻ ስራዎችን በማከናውን እቅዱን ለማሳካት ሰፊ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ መሬት ላይ የሚኖሩ ሁኔታዎች ወሳኝ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ስራውን የሚቻለውን ያህል በተሰጠው የ3 አመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረቶችን እያደረገ ነው፡፡

ይህ እንተጠበቀ ሆኖ ምክክር የሚጠይቀውን ጊዜና ኡደት በተመለከተ የተዛቡ አረዳዶችም መኖራቸውም ከጊዜ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥቄዎች ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በምክክር ኡደት ሰፊውን ጊዜ /በአንዳንድ ጥናቶች ከ70-80 በመቶውን / የሚወሰዱት ከምክክር በፊት ያሉ ምዕራፎች ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት ሰፊ ጊዜ የወሰዱ ሳይሆኑ የሚገባቸውን ያህል ጊዜ የወሰዱ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡

በሌላም በኩል እንደ ኢትዮጵያ በበርካታ እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሰፊ የሀሳብ ልዩነቶች ባሉበት ሀገር ሁሉ ነገር በ3 አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ብሎ መገመቱም አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢያንስ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ምክክሩ ተጀምሮ መግባባት ላይ ከተደረሰ ሌሎች ጉዳዮችም በሂደት መፍትሄ እያገኙ ይሄዳሉ፡፡ ይህም የሀሳብ ልዩነቶችን ወይም አለመግባባቶችን በምክክር የመፍታት ባህል እየገነቡ ለመሄድ ያስችላል፡፡ ይህም ቀጣይነት ባለው መልኩ በተራዘመ ጊዜ መከናወን ያለበት ተግባር ነው፡፡

Other Section

በሀገራዊ ምክክሩ እነማን እንዴት ይሳተፋሉ?

 

1st የወረዳ ተሳተፊዎች
የወረዳ ተሳተፊዎች

 

2nd በክልል ከተማ አስተዳደርደረጃ የምክክሩ ሂደት ተሳታፊዎች
 በክልል ከተማ አስተዳደርደረጃ የምክክሩ ሂደት ተሳታፊዎች

 

3rd በፌደራል ደረጃ የምክክሩ ሂደት ተሳታፊዎች
ፌደራል ደረጃ የምክክሩ ሂደት ተሳታፊዎች

 

 

ተጨማሪ ያንብቡ

የሀገራዊ ምክክር የአሰራር ሥርአቶችና መመሪያዎች

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋሚያ አዋጁ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 9 ላይ የጽህፈት ቤቱን የውስጥ የአሠራር ሥርዓት፣ የምክክር አጀንዳዎች ወይም አርዕስት የሚመረጡበትን የሚመለከት፣ በሀገራዊ ውይይቶች ላይ የሚሳተፉ አካላት የሚለዩበትን ሥርዓት ለመዘጋትና መሰል ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችሉ ውስጠ ደንቦችን እና መመሪያዎችን በማውጣት በሥራ ላይ እንደሚያውል ተደንግጓል፡፡

በዚሁም መሠረት የምክክር ሂደቱን ግልጽ፣ አሳታፊና አካታች ለማድረግ የሚረዱ የተለያዩ የአሰራር ስርአቶችንና ውስጠ ደንቦችን በማዘጋጀት ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የአሰራር ሥርዓቶቹ ከባቢያዊና ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ በማስገባት ተገቢውን ማስተካከያ በማድረግ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡

ተሳታፊዎችን ለመለየት እና አጀንዳ ለማሰባሰብ የተዘጋጀ አሰራር ስርዓት

 

የአጀንዳ ሀሳብ ይስጡ

የአጀንዳ ሀሳብ ካልዎት እባክዎ በአጭር ጽሁፍ ወይም በ PDF ወይም MS-Word አድርገው በተከታዩ ፎርም  ይላኩልን፡፡

እናመሰግናለን፡፡

የምክክር አጀንዳ ይስጡ – Send Dialogue Agenda

ስለ ሀገራዊ ምክክሩ ምን ተባለ?

ስለ ሀገራዊ ምክክሩ ምን ተባለ?

ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ- “የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ያደርጋል።”

https://www.youtube.com/watch?v=MtVYoehgODU

———————–

አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ- “ሀገራዊ ምክክሩ የታሰበለትን አላማ በማሳካት ውቴታማ እንዲሆን የሕዝብ ተሳትፎ መጠናከር አለበት።”

https://www.youtube.com/watch?v=5RVkQt1Uklg

———————–

አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ- “ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉን አካታች ለማድረግ መስራት ይገባል፡፡“

https://www.youtube.com/watch?v=BKnb7JfypHI

———————–

 

ራሄል ባፌ (ዶ/ር)- “እኛ የሕዝቡን አጀንዳ የመወሰን መብት የለንም፡፡ ይህ አካሄድ ነው ኢትዮጵያን እስካሁንም የገደላት፡፡”

https://www.youtube.com/watch?v=Yj9tfqy7tEk

———————–

ቻላቸው ታረቀኝ- “የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር- በሰጥቶ በመቀበል መንፈስ እውነተኛ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ሁሉም ወገን ዝግጁ መሆን አለበት።”

https://www.youtube.com/watch?v=Vi6LPSkKUOk

———————–

ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ሥላሴ- “በምክክሩ መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮችን መንግስት ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጫ አግኝተንበታል፡፡”

https://www.youtube.com/watch?v=1rc2HqRatOA

———————–

ዴስቲኒ ኢትዮጵያ- “ሀገራዊ ምክክሩ በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ዋነኛ መፍትሔ ነው።”

https://www.youtube.com/watch?v=pY0zm89P-P8

የሀገራዊ ምክክር ምክረ ሀሳቦችና አተገባበር

ምክረ ሀሳቦችና አተገባበር

የሀገራዊ ምክክር ውጤቶችን በአግባቡ መረዳት፣ የተገኙ ውጤቶች ተግባራዊ የሚሆኑበትን ዝርዝር ዕቅድ ማዘጋጀትና ስልቶችን መንደፍ እንዲሁም ለትግበራው ምዕራፍ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት አተገባበሩን መከታተል ትኩረት የሚሰጣቸው አንኳር ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሀገራዊ ምክክር ትልቅ የሽግግር ፍኖተ ካርታ አካል ሆኖ በኢኮኖሚ፣ በመዋቅራዊ፣ በፖለቲካ እና በፍትህ ማሻሻያ ሂደቶች መታጀብ አለበት። ሀገራዊ ምክክሮች በራሳቸው ፍጻሜ ሳይሆኑ የተቀናጀና አሳታፊ የለውጥ ሂደት ጅምር መሆናቸው መታወቅ አለበት።

 

የምክክር ሂደት የመጨረሻው ምዕራፍ በምክክሩ መግባባት የተደረሰባቸውን ምክረ-ሀሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ እንደ ምክረ-ሀሳቦቹ ባህርይ ተግባራዊነታቸው በአጭር፣ በመካከለኛ ወይም በረዥም ጊዜ ተፈጻሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የሚተገበሩበት ፍጥነትና ስፋት እንደ ምክረ-ሀሳቦቹ ባህርይ ብቻም ሳይሆን ለተግባራዊነቱ ባለድርሻ የሆኑ አካላት እንደሚያደርጉት ጥረትና እንደሚኖራቸው ቁርጠኝነትም ሊለያይ ይችላል፡፡

የሚደረገው ጥረትና የሚኖረው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ሲሆን፡ በአጠረ ጊዜና በምልዓት ተግባራዊ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ የተግባራዊነቱን ሰፋትና ፍጥነትን የመወሰን አቅም ያለቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በዋናነት ግን መገባባት ላይ የተደረሰበት መንገድ፣ አሳታፊነቱ፣ አካታችነቱና ግልጸኝነቱ ወሳኝ መነሻዎች ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ሂደቱ ቅቡልነት ያለውና መሠረተ ሰፊ የሆነ መግባባት ላይ ከተደረሰ አተገባበሩ ሰፊና ፈጣን የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ የአስፈጻሚውን አካል የቤት ስራም ቀላል ያደርገዋል፡፡ በሌላም መልኩ አስፈጻሚው አካል የሕዝቡን ፍላጎት ተረድቶና አክብሮ ተግባራዊ እንዲያደርግ ተጽእኖ የመፍጠርን ጉልበት ያገኛል፡፡ ይህም በመሆኑ ነው በሀገራዊ ምክክር ላይ ከውጤቱ ይልቅ ሂደቱ ጤናማ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት መደረግ ያለበት፡፡

ሀገራዊ ምክክሮች ከመመካከር ሂደት ባሻገር በተግባር ላይ በሚውሉ መርሆች ላይ ተመስርተው የሚመቻቹ ሂደቶች ናቸው። የትግበራው ምዕራፍ የተለያዩ ተግዳሮቶችን እና ዕድሎችን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ በምክክር ሂደት ላይ መሳተፍ በራሱ የሚያመጣቸው ማህበራዊ በበጎ ልምምዶች እንደተጠበቁ ሆነው መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ሀሳቦች ወደ ተግባር ተለውጠው መታየት ይኖርባቸዋል፡፡

በወቅቱ ከተፈጠሩና መሰረታዊ ልዩነቶች ናቸው ተብለው በምክክር ሂደት መግባባት ከተደረሳበቸው አጀንዳዎች በተጨማሪ ቀሪ ጉዳዮችን ወይም በቀጣይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አዳዲስ የልዩነት ሀሳቦችን ቀጣይነት ባለው የምክክር ሂደት ለመፍታት እንዲቻል ለቀደመው ሀገራዊ ምክክር ተገቢውን ዋጋና ክብር በመስጠት የተደረሰባቸው መግባባቶች ተግባራዊ እዲሆኑ መደረግ አለበት፡፡

በምክክር ሂደቱ መግባባት ላይ መደረሱን እንደ መጨረሻ ውጤት በመውሰድ የሚመለከታቸው ወሳኝ ባለድርሻ አካላት ትኩረታቸውን እንዳይቀንሱ የሚያደርጉ ተግባራት አስቀድመው መታቀድና በየወቅቱ እና በየደረጃው መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም ለተፈጻሚነታቸው ዝርዝር የአፈጻጻም ዕቅድ ማዘጋጀት፣ ህዝቡና ባለድርሻ አካላት በቂ ግንዛቤ አግኝተው በሂደቱ እንዲቀጥሉበት መበረታታት እንዲሁም በሂደቱ የተገኙ የመከባበር፣ የመተባባርና የመተማመን ተሞክሮዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያደርጉ ስራዎች ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

በጥቅሉ የሀገራዊ ምክክሮች ውጤቶች በሁለት ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ተጨባጭ (tangible) እና የማይዳሰሱ (intangible)፡፡ ተጨባጭ የሆኑ ውጤቶች ምክክር በተደረገባቸው አጀንዳዎች ላይ የተደረሰባቸው መግባባቶች ናቸው፡፡ በስምምነቶች፣ በሪፖርት ወይም በመግለጫ እና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክረሃሳቦችን በማካተት ሊገለጹ ይችላሉ።

የሀገራዊ ምክክር ሂደት ተጨባጭ ውጤቶች በተቋማዊና “በሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ” ፣ በፖለቲካ፣ በፍትሕ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችና ግንባታዎች ዙሪያ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ ምክረ ሀሳቦችን ያካትታሉ። ሁለተንናዊ ለሆነ አዲስ ለውጥ ፍኖተ ካርታ የመሆን አቅምም አላቸው፡፡ ተጠባቂው ውጤት እንደየሀገራዊ ምክክሩ አላማዎች የተለያየ ነው፡፡ በአንዳንድ ሀገራት በተደረጉ ሀገራዊ ምክክሮች ህገ መንግስታዊ ለውጥ፣ የአዲስ መንግስት ምስረታ ወይም የስልጣን ክፍፍል፣ የሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች መከበር፣ የሰላም መስፈን፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞች እንዲሁም ማህበራዊ ፍትህን አስገኝተዋል፡፡

ከማይዳሰሱ የምክክር ሂደት ውጤቶች መካካል በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል የግንኙነቶች ለውጥ እና በቀጣይነት ሊጠናከር የሚችል በልዩነቶች ዙሪያ በሰከነ መንገድ የመነጋገር ባህል ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ውጤቶች፣ ከሂደቱ ባሻገር እንዲዳብሩ ከተደረጉ በሰፊውና ረዥሙ የለውጥ ሂደት ውስጥ አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው።

እዚህ ላይ ሁለቱም ዓይነት ውጤቶች አስፈላጊና ተመጋጋቢ መሆናቸውን መገንዘቡ ጠቃሚ ነው፡፡ የማይዳሰሱ ውጤቶች ፖለቲካዊ ሽግግርን ከማሳለጥ፣ ቀውሶችን ከመቅረፍ፣ ልዩነቶችን ከማጥበብ በተጨማሪ ለመሠረታዊ ማኅበራዊ ለውጥ መሠረት የመጣል አቅም አላቸው፡፡ ከዚህም በላይ የማይዳሰሱ ውጤቶች ተጨባጭ ውጤቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

በምክክር ሂደቱ የተገኙ ውጤቶች የአተገባበር ምዕራፍ ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ እና ዲዛይን ያስፈልገዋል፡፡ እንደ ሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ እና ተልዕኮ፣ የትግበራ ዕቅዱ መዘጋጀት ያለበት ምክክሩ ሲጠናቀቅ ሳይሆን በሂደት ላይ ቢሆን የበለጠ ውጤታማ እንደሆነ ይታመናል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከምክክሮቹ የሚያጠቃልላቸውን ምክረ ሀሳቦች በመቀመር አፈጻጸሙን የተመለከተ ዝርዝር ዕቅድ ለሚመለከተው አስፈጻሚ አካል የማቅረብ እንጂ የማስፈጸም ተልዕኮ አልተሰጠውም፡፡ ይህም መሆኑ በአንዳንድ ወገኖች “የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦች የመፈጸም ዕድላቸው በአስፈጻሚው አካል በጎ ፈቃደኝነትና ጥረት ላይ የተንጠለጠሉ መሆናቸው ክፍተት ይፈጥራል” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሀገሪቱ በርካታ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ የሆኑ ልዩነቶች እንደመኖራቸው መጠን የሚደረስባቸውን መግባባቶች ተግባራዊ ለማድረግ ከመንግስት የተሻለ ተቋማዊ ቁመናም ሆነ አቅም ያለው አካል ባለመኖሩ ቁርጠኝነት ካለው በተሻለ ሊፈጸም የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህ መካከል ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ የተደረሰባቸውን ድምዳሜዎችና ምክረ ሀሳቦች ለህዝብ በይፋ የማሳወቅ ስልጣን ያለው መሆኑ ትልቅ ጉልበት እንደሚሆነው ይታመናል፡፡ ይህ መሆኑ ህዝቡና ባለድርሻ አካላት በአስፈጻሚው አካል ላይ ተገቢውን ግፊት በማድረግ ምክረ ሀሳቦቹ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የማድረግ እድል የሚሰጠው ከመሆኑም በላይ ለተግባራዊነታቸውም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡

በአንጻሩም በስልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚዎች ዘንድ በሀገሪቱ እጅግ መሰረታዊ በሆኑ በርካታ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች መኖራቸው ሀገረ መንግስቱን ለማጽናት፣ ሰላምን ለማስፈን፣ ልማትና ዴሞክራሲን ለማፋጠን ለሚደረገው ጥረት አለመፋጠን ተግዳሮት መሆኑን የሚረዱ በመሆናቸውና እነዚህኑ ተግዳሮቶች ማስወገድ በህዝቡ ዘንድ ቅቡልነትን ለማግኘት ወሳኝ ጉዳይ እንደሚሆን ይገነዘቡታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም ፖለቲካዊ አንደምታው ከፍ ያለና ገሸሽ ሊደረግ የሚችል አይሆንም፡፡

በሌላም በኩል በኢትዮጵያ እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንዲደረግ ፖለቲካዊ ፍላጎቱን ምክክር ኮሚሽኑን በአዋጅ በማቋቋም የገለጸው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት፤ መግባባት ላይ ለሚደረስባቸው ጉዳዮች ተፈጻሚነትም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱ እንዳለው በተለያዩ ወቅቶች መግለጹ እንደ ተጨማሪ አቅም የሚወሰድ ነው፡፡

የአፈፃፀሙ ምዕራፍ አስፈላጊው ገጽታ ሀገር አቀፍ ባለድርሻ አካላት የምክረ ሀሳቦቹን ዝርዝር ሁኔታ እንዲከታተሉ እና ያልተፈቱ ወይም ችግር ያለባቸው ጉዳዮች እንዲፈቱ ተገቢውን ጥረት እና በአስፈጻሚው አካል ላይ አስፈላጊውን ግፊት ማድረግ የሚያስችል ስረዓት መኖሩ ነው።

ቅሬታ/ጥቆማ አልዎት?