የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

“ሀገራዊ ችግሮችን ከሥረ መሠረታቸው ለመፍታት ሴቶች ያላቸው ክህሎት የላቀ ነው!” ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ

blank 4 grids collage

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “በሀገራዊ ምክክሩ የሴቶች ተሳትፎና ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ አካሄደ፡፡

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ፤ ሀገራዊ ምክክር በአካታችነት መርህ የሚመራ መኾኑን ማረጋገጥ ለዘላቂ ሰላም ጠቃሚ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግጭቶችና ሥር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት ከሀገራዊ ምክክር ሌላ መፍትሔ እንደሌለም ገልጸዋል።

ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የሚሳተፉት መብታቸው ስለኾነ ብቻ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ችግሮችን ከሥረ መሠረታቸው ለመፍታት ያላቸው ማኅበራዊ ክህሎት የላቀ በመኾኑም ጭምር እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቷ አክለውም መወያየት ብቻውን ግብ አይደልም፤ ውጤት የሚያመጣው ተግባራዊነቱ ሲረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኮሚሽኑ አካታችና አሳታፊ የምክክር ሂደት እንዲኖር የሚያስችል የአሠራር ሥርዐት መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡

ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ከኮታና ቁጥር ባሻገር በሀሳብም እንዲወከሉ ማድረግ፤ የምክክሩን ሂደት ሙሉ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተሥፋዬ በበኩላቸው፤ ከሀምሳ በመቶ በላይ የሀገሪቱን ቁጥር የሚሸፍኑት ሴቶች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ችላ መባል እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡

የሴቶች ተሳትፎ ለሀገራዊ ሰላምና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ገልጸው፤ ሴት የምክርም፣ የምክክርም ጥበብ ስላላት ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ የሥርዐተ ጾታን ፍትሐዊነት በማረጋገጥ አካታችና አሳታፊ እንዲኾን ሴቶች 30 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው በተሳታፊ ልየታ የአሠራር ሥርዐተ ውስጥ አካቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

blank 4 grids collage