በትግራይ ክልል አስቻይ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በክልሉ ምክክር ለማካሄድ ኮሚሽኑ ዝግጁ ነው፤ አስቻይ ሁኔታ እስኪፈጠር በአዲስ አበባ ይካሄዳል“- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት የሀገራዊ ምክክር ተሳትፎ ጥሪን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ፤ ኮሚሽኑ በመላ ሀገሪቱ ከወረዳ ጀምሮ በርካታ ተግባራትን አከናውኖ ተጨባጭ ስኬቶችን አስመዝግቧል ብለዋል፡፡
ትግራይ ክልል በምክክር ሂደቱ በምልአት መሳተፍ እንዳለበት ኮሚሽኑ በጽኑ እንደሚያምን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ የኮሚሽኑ የአሠራር ሥነ ዘዴ በዚህ መልኩ የተቃኘ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በትግራይ በክልል ምክክሩን ለማከናወን ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከሲቪክ ማኅበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እና ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር 22 የውይይት መድረኮች መደረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ምክክር ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ አለመኖሩን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ አስቻይ ሁኔታ እስከሚፈጠር ከክልሉ ከሚመጡ ባለድርሻ አካላት እና በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ጋር በአዲስ አበባ አጀንዳ የማሰባሰቢያ መድረክ ለማከናወን የኮሚሽኑ ምክር ቤት መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም መሠረት የትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት በተወካዮቻቸው አማካኝነት የሚሳተፉበት የአጀንዳ ማሰባሰብና የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ተሳታፊዎች ልየታ መድረክ ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ ፕሮፌሰር መሥፍን ይፋ አድርገዋል፡፡
አስቻይ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ደግሞ እንደ ሌሎች ክልሎች ሁሉ በክልሉ የምክክር መድረኮች እንደሚከናወኑም ዋና ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል፡፡
በዚህ ምክክር እንዲሳተፉ ጥሪ የተደረገላቸው የክልሉ ባለድርሻ አካላት ለምክክሩ ስኬት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም ዋና ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡
መግለጫውን ተከትሎ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች በኮሚሽሮች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡





