የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

54 የሚዲያ ተቋማት፤ 461 ጋዜጠኞች የምክክሩን ሂደት እየዘገቡ ነው

4d7a5608

54 የሚዲያ ተቋማት፤ 461 ጋዜጠኞች የምክክሩን ሂደት እየዘገቡ ነው
ነሀሴ 3/2018 ዓ.ም
ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ያለውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለመዘገብ ፍላጎት ኖሯቸው ከኮሚሽኑ ጋር ግንኙነት የፈጠሩ 54 የሚዲያ ተቋማት 461 ዘጋቢዎችን በጉባኤው ቦታ አሰማርተው የጉባኤውን ሂደት ለህዝብ እያደረሱ ይገኛሉ፡፡
የሚዲያ ተቋማትን የዘገባ ተሳትፎ እና የመረጃ ተደራሽነትን በተመለከተ ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ሪፖርት እንዳመለከተው ኮሚሽኑ ሀገራዊ ምክክሩ ከመካሄዱ በፊት በርከት ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫና የአጋርነት ማጠናከሪያ መድረኮችን ከመገናኛ ብዙሃን ሀላፊዎችና ባለሙዎች ጋር አካሂዷል፡፡
በእነዚህ መድረኮች በተፈጠረው ግንዛቤና በተደረሰው መግባባት በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት በርካታ የሚዲያ ተቋማት እና ባለሙያዎች እንዲሳተፉ መደላድል ከመፍጠሩ ባሻገር መረጃዎች በሙያዊና ሀገራዊ ሃላፊነት እንዲሰራጩ ማስቻሉን በዚሁ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡
ተሳትፎው ሁሉንም የመገናኛ ብዙሃን አይነቶች እንዳካተተ እንዲሁም የተቋማቱን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ባከበረ መልኩ መረጃዎችን ተደራሽ የሚያደርጉበት ነፃነት በኮሚሽኑ በኩል የተረጋገጠ መሆኑንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ኮሚሽኑ በምክክሩ ቦታ ተገኝተው እንዲሁም ከኮሚሽኑ ማህበራዊ ሚዲያ ገፆች እና በስፍራው ከሚገኘ መገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን እየተጋሩ ለህዝብ እያደረሱ ላሉ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርቧል፡፡ ይህንን ተሳፎ እስከ ድህረ ምክክር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ተጠይቋል፡፡
ህብረተሰቡ ወደ ምክክሩ ቦታ እየገቡ መረጃዎችን ተደራሽ ከሚያደርጉ መገናኛ ብዙሃንና ባለሙያዎች መረጃዎችን በማግኘት ከተዛቡ መረጃዎች ራሱን እንዲጠብቅም ኮሚሽኑ አስገንዝቧል፡፡
ኮሚሽኑ ይህንን ሪፖርት ያስደመጠው ከተለያዩ የዘርፉ ተቋማት ለተውጣጡና ኮሚሽኑን እየደገፉ ላሉ የሚዲያ ስራዎች አጋዥ አካላት ነው፡፡