ብሔራዊ ጥቅም በሀገራዊ ምክክር ሂደት
የካቲት 24/2016 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በተመሰረበት አዋጅ 1265/2014 ላይ ብሔራዊ ጥቅም ከኮሚሽኑ መርሆዎች አንዱ ተደረጎ ተደንግጓል፡፡ እዚህ ላይ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች እና ተጠባቂ ውጤቶች የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም በምን መልኩ ሊያስጠብቁ እንደሚችሉ ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡
ሀገራት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሲያልፉ ሊያሳኩ የሚሹት በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል ያሉ መሰረታዊ የሀሳብ ልዩነቶችን በመፍታት እና ሀገራዊ መግባባትን እንዲፈጠር በማድረግ ጠንካራ ሀገረ መንግስትን መገንባት ነው፡፡ ለዚህም ነው ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ በአዋጁ ውስጥ ዋነኛ ጉዳይ ሆኖ የተደነገገው፡፡ በዚህ ረገድ የሀገራዊ ምክክር ሂደት የአንድን ሀገር ብሔራዊ ጥቅም እንዴት እንደሚያስጠብቅ ከዚህ በመቀጠል ይቀርባል፡፡
- የጋራ ግብ ያላቸውን ባለድርሻ አካላት ማሰባሰቡ
በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሀገሪቱ ላይ ተንሰራፍተው በሚገኙ የጋራ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ምክክር ያደርጋሉ፤ መፍትሔዎቻቸውም ላይ ይመክራሉ፡፡ በሂደቱ ባለድርሻ አካላቱ ስለሀገራቸው ሰላም፣ ልማት፣ ፍትህ፣ ወዘተ መነጋገራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በጋራ የሚስማሙባቸው መፍትሔዎች እየነደፉ ይሄዳሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮችም የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በአጀነዳነት የሚነሱ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
- የተፈጠሩ ቅራኔዎች እንዲፈቱ ማስቻሉ
ሀገራዊ ምክክር በተለያዩ ቡድኖች መካከል የተፈጠሩ ቅራኔዎች በውይይት እንዲፈቱ በማድረግና አንዱ የሌላውን ጉዳይ በመስማት ይበልጥ መቀራረብ እንዲፈጠር ያስችላል፡፡ በሂደቱ ላይ የሚሳተፉ አካላት ይህንን ማድረጋቸው አንድነትን ለማስጠበቅ የራሱን ሚና የሚጫወት ሲሆን የአንድ ሀገር ዜጎች የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉም አመላካች ነው፡፡ ይህም የውጪ ጣልቃ ገብነትን ተከላክሎ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቁ ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
- የሀገር ሉዓላዊነትን እና መረጋጋትን ማጠናከሩ
በመርህ ደረጃ ሉዓላዊነትዋ የተከበረ እና የተረጋጋች ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞቿን ማስጠበቅ ትችላለች፡፡ ሀገራዊ ምክክር በተለያዩ የፖለቲካና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች እንዲፈቱ በማስቻል ለውጭ ጣልቃ ገብነቶች ጋባዥ የሆኑ ግጭቶችን ለማስቀረት ይሰራል፡፡ ይህም የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና የሚኖረው ሲሆን ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበርም የዚሁ ተጓዳኝ ውጤት ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡
- በተቋማት ላይ እምነት እንዲገነባ መስራቱ
ከሀገራዊ ምክክር ሂደቶች የሚገኙ ምክረ-ሀሳቦች በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ ተቋማት የፖሊሲ ማሻሻያ ግብዓት ሆነው ሊያገግሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ በእነዚህ የፖሊሲ ማሻሻዎች ተጠቃሚ የሚሆኑ ተቋማት በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተዓማኒነት እና ቅቡልነት እንዲገነቡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ይህም ሀገራችን በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ተያያዥ ጉዳዮች ልታገኛቸው የሚገቡ ብሔራዊ ጥቅሞችን እንዳታጣ ከፍተኛ እገዛን ያደርጋል፡፡
- ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦች በተለያዩ ዘርፎች እንዲመነጩ ማስቻሉ
ብሔራዊ ጥቅም በባህሪው ዘላቂ የሆኑ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወዘተ ጉዳዮች የሚነሱበት ሀገራዊ ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ሀገራዊ ምክክርም በእነዚህ ዘርፎች ውስጥ የሚስተዋሉ የእኩልነት ጥያቄዎችን፣ ብልሹ አሰራሮችን፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን፣ ፖለቲካዊ አካታችነትን ወዘተ ተነስተው ምክክር እንዲደረግባቸው እና የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርስባቸው አበክሮ ይሰራል፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!