የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የጤናው ማህበረሰብ ለምክክሩ ስኬት የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

img 20260207 122850 355

የጤናው ማህበረሰብ ለምክክሩ ስኬት የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

ጥር 30/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ስር ለሚገኙ የጤና ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ አድርጓል።

የከተማው ጤና ቢሮ ባዘጋጀው መድረክ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) የኮሚሽኑን የስራ እንቅስቃሴና የምክክሩ ሂደት የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።

ኮሚሽኑ ያለ መግባባት መንስኤ የሆኑ እጅግ መሰረታዊ ጉዳዮችን በህዝባዊ ውይይቶች መለየቱን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፥ እስካሁን ከትግራይ ክልል በስተቀር በመላ ሀገሪቱ እንዲሁም በተወሰኑ የውጪ ሀገራት በመዘዋወር ስኬታማ ስራ መስራቱን አንስተዋል።

በትግራይ ክልል ምክክር ማካሄድ፣ ሀገራዊ ጉባኤ መጥራት ቀሪ የኮሚሽኑ ዐበይት ተግባራት እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በሀገራችን ችግሮችን በነፍጥ አማራጭ ለመፍታት ሲሞከር እንደቆየ ጠቁመው ይህ አካሄድ ውጤት አለማስገኘቱን አውስተዋል።

እንደ ዋና ኮሚሽነሩ ገለፃ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ምክክር ብቸኛው አማራጭ ነው።

የጤና ተቋማት በርካታ ተገልጋዮችን የሚያስተናግዱ በመሆኑ አመራሮችና ባለሙያዎች ስለ ኮሚሽኑ ስራና ስለ ምክክሩ ሂደት በቂ ግንዛቤ ማዳበራቸው በተገልጋዮች ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ ይህ ገለፃ የቀረበላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች በየተቋሞቻቸው ለሚገለገሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ዘዴዎች ስለምክክሩ ሂደት በማስገንዘብ ኮሚሽኑን እንዲያግዙም ዋና ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ባዘጋጀው በዚህ መድረክ በከተማዋ ከሚገኙ ሁሉም ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የመጡ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥር 6/2018 ዓ.ም ባዘጋጀው የቁልፍ ባለ ድርሻ መድረክ ጤና ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ተገኝተው የኮሚሽኑን ስራ ለማገዝ መግባባት ላይ መድረሳቸው አይዘነጋም።