የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡

cropped favicon.png
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የ2016 ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መጠናቀቅን በማስመልከት መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ በመገለጫው ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሚመለከት ጉዳይ ይገኝበታል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ “የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት አዋጅ አኳያ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ ሁኔታ ሀገራዊ ችግሮችን በምክክርና በውይይት ለመፍታት የተቋቋመ መሆኑን” ጉባኤው መረዳቱን ገልጾ ቤተክርስቲያኒቱ በኮሚሽኑ በኩል በይፋ የቀረበ የተሳትፎ ጥሪ እንዳልተደረገላት በመግለጽ በሂደቱ ቅር መሰኟቷንና ከዚህም በመነሳት “የቤተ ክርስቲያኒቱ ተሳትፎና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ከኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ተከታትሎ ለፍጻሜ የሚያበቃ” ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ መሰየሙንም ከጉባኤው መግለጫ ለመረዳት ችለናል፡፡
በቅድሚያ የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ ለሀገራዊ ምክክሩ ትኩረት በመስጠት በመምከሩና ቅሬታ ያሳደሩ ጉዳዮችንም ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት በመወያየት ለመፍታት መወሰኑን በአክብሮት የምንመለከተው ጉዳይ ነው፡፡
ኮሚሽኑ ገና ሥራውን እንደጀመረ የመግባቢያ ሠነድ የተፈራረመው ከአምስቱ ተባባሪ አካላት አንዱ ከሆነው ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር ነው፡፡ ኮሚሽኑ ሌሎች ተባባሪ አካላትን ጨምሮ ከጉባዔው ጋር ከመነሻው ጀምሮ በትብብር በመሥራት ላይ ይገኛል።
በተበባሪ አካላት ሥልጠና፣ በተሳታፊዎች ልየታ እንዲሁም በቅርቡ በተካሄደውና በስኬት በተጠናቀቀው በአዲስ አበባ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ሂደት ጉባዔው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል። ከዚህም ባሻገር ኮሚሽኑ በሸራተን አዲስ ሆቴል እራሱን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሲያስተዋውቅ ጀምሮ ቤተክርስቲያኒቱን በመወከል በየወረዳው፣ በዞንና በክልሎች በተካሄዱ መርሐግብሮች በሙሉ በጸሎትና ቡራኬ በመስጠት የተሰራው ስራ የሚዘነጋ አይደለም።
በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ የምንወደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ኮሚሽኑ ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው ጋር በተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት የሌሎች የእምነት ተቋማትን ከሚወክሉ ተወካዮች ጋር በመሆን በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ካሉ ሀገረ ስብከቶቿ የሀይማኖት መሪዎችን በመመደብ የተሳታፊ ልየታው ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታደርግ መቆየቷን ነው። ለዚህም አስተዋጽኦዋ ኮሚሽኑ ልባዊ ምስጋናውን ለማቅረብ ይወዳል፡፡
በመጨረሻም ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር ቅዱስ ሲኖዱሱ ጽ/ቤት ድረሰ በመገኘት ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን እየገለጸ ይህ የአካታችነት መርህ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ጋር በእኩልነት የሚተገበር መሆኑን በታላቅ አክብሮት ያስታውቃል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ግንቦት 29 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባcropped favicon.png