ወደ ስዊድን ያቀናው የኮሚሽነሮች ልዑክ ከዳያስፖራ ኮሚዩኒቲ አደረጃጀቶች ጋር ተወያየ
መስከረም 21/2018 ዓ.ም
በኖርዲክ አገሮች ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብ እና በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ የዲያስፖራ ተወካዮችን ለማስመረጥ ወደ ስዊድን የተጓዘው የኮሚሽነሮች ልዑካን ቡድን በስዊድን የተለያዩ ከተሞች ከሚገኙ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች እና የኃይማኖት አባቶች ጋር ተወያይቷል፡፡
ቡድኑ ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራትና የቀጣይ አቅጣጫዎቹን በተመለከተ ለአደረጃጀቶቹ ገለፃ አድርጓል፡፡
በመጪው ቅዳሜ መስከረም 24/2018 ዓ.ም በስዊድንና በአካባቢው አገራት ከሚኖሩ የኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ ለማሰባሰብና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች ለመለየት የውይይት መድረክ እንደሚያካሂድም ለአደረጃጀቶቹ አስገንዝቧል።
የዲያስፖራ አደረጃጀት አመራሮች በቀጣይ ቅዳሜ የሚደረገው የውይይት ሂደት አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ያቀረቡ ሲሆን ኮሚሽነሮች በተነሱ ጉዳዮች ላይ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መድረኩ ሀገራዊ ፋይዳቸው የላቀ አጀንዳዎች የሚሰበሰቡበትና የተሳካ እንዲሆን በአካባቢው የሚገኙ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ኮሚሽኑን እንዲያግዙ ተጠይቋል።
አደረጃጀቶቹ እራሳቸው በምክክር መድረኩ በንቃት እንዲሳተፉና በስካንዲኔቪያ የሚገኙ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንዲሳተፉ በማስተባበርና በቅስቀሳ እንዲያግዙ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።
ኮሚሽኑ በስዊድንና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ የሚያሰባስብበት እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች የሚለይበት የምክክር መድረክ በመጪው ቅዳሜ መስከረም 24/2018 ወይም ኦክቶበር 4/2025 ከጠዋቱ 9፡00 AM ጀምሮ በስቶክሆልም Stockholmsmässan AB SE-125 80 Stockholm የሚካሄድ ይሆናል።





