የአካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ላይ በንቃት የመሳተፋቸው አስፈላጊነት
ህዳር 24/2017 ዓ.ም
የሀሳብ ልዩነቶች የሰላም እጦትን፣ ግጭትን እና መፈናቀልን ሲያስከትሉ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚጎዱ ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው፡፡ በተለይም የዚህ ጉዳት ዋነኛ ሰለባዎች የአካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የአካል ጉዳተኞች የሚገኙ ሲሆን እነሱም በሀገራችን የስነ-ህዝብ ምጣኔ ከአንድ አስረኛ በላይ እንደሚሆኑ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
እነዚህ ወገኖቻችን በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ በንቃት መሳተፋቸው ለእነሱ ምቹ የሆነች ሀገርን በመገንባቱ ረገድ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ቁልፍ ተዋንያን እንዲሆኑ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቶቹ ላይ የሚሳተፉ የአካል ጉዳተኞችን ቢያንስ በ10% ተወክለው የወከላቸውን የሕብረተሰብ ክፍል ሀሳብ በአደራ ይዘው ለኮሚሽኑ እንዲቀርቡ ኮሚሽኑ የአሰራር ስርዓቶችን ዘርግቷል፡፡
ለመሆኑ የአካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ በንቃት መሳተፋቸው ምን አይነት ጥቅም አለው?
- በሂደቱ ላይ ሊኖራቸው የሚገባውን የውክልና ኮታ በመጠቀም ድምፃቸውን ለማሰማት ምቹ አጋጣሚን ይፈጥርላቸዋል፡፡
- በሂደቱ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ሀሳቦችን በማቅረብ ለፖሊሲ ማሻሻያነት በግብዓትነት ሊቀርቡ ያስችላቸዋል፡፡
- በሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ መብቶቻቸውን በውይይት የማስከበርን ዲሞክራሲያዊ ባህል ያጎለብትላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!