የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የዲያስፖራ ማህበር አባላት ጋር ህዳር 8 ቀን 2016 ዓ. ም በሚሊኒየም አዳራሽ ውይይት አድርጓል፡፡ የውይይት መድረኩ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባ ንቁ ተሳትፎ እና ሊያደርጉ ስለሚገባው ድጋፍ ግንዛቤን ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡
መርሐ-ግብሩም በኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፈሰር መስፈን አርያአያ የመክፈቻ ንግግር የተከፈተ ሲሆን በሀገር ውስጥ የሚኖሩ የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት የሀገራዊ ምክክሩ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ የዲያስፖራ አባላት የተሳተፉበት ይህ መድረክ የተለያዩ መርሐ-ግብሮችን አስተናግዷል፡፡ በዚህም መሰረት ስለ ሀገራዊ ምክክር መሰረታዊ ፅንሰ ሀሳብ፣ በኮሚሽኑ ስለተከናወኑ ተግባራት እና ኮሚሽኑ ስለሚገዛባቸው የህግ ማዕቀፎች ገለፃ እና ማብብራርያ በኮሚሽኑ አባላት ተሰጥቷል፡፡
ገለፃውን ተከትሎ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን የዲያስፖራው ማህበረሰብ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር ስለሚሰራባቸው መንገዶች ሀሳብ እና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡ ከዚያም ባሻገር ኮሚሽኑ በሀገር ውስጥ ከሚኖሩ የዲያስፖራ አባላት ጋር ግንኙነቱን በማጠናከር አካታችነትን ማረጋገጥ እንደሚገባው ተጠቁሟል፡፡