የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ኮሚሽኑ በአፋር ክልል ለሚገኙ ተባባሪ አካላቱ ከመስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡

afar

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል ለሚገኙ ተባባሪ አካላቱ ከዛሬ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ስልጠና መስጠት ጀመረ፡፡ በክልሉ ከሚገኙ 48 ወረዳዎች ለተውጣጡ 380 ሰልጣኝ ተባባሪ አካላት በሰመራ ከተማ እየተሰጠ የሚገኘው ይህ ስልጠና ተባባሪ አካላቱ በየወረዳቸው ከሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ተሳታፊዎችን በመለየት ሂደት ውስጥ ለኮሚሽኑ እገዛ እንዲያደርጉ አቅማቸውን ለማጎልበት ታስቦ ነው፡፡

በአፋር ክልል ኮሚሽኑ ከየማህበረሰብ ክፍሉ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊዎችን ሲለይ ለኮሚሽኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ እየሰለጠኑ የሚገኙ ተባባሪ አካላት ምልመላ የአካባቢውን ዓውድ ከግምት ያስገባ ሲሆን የጎሳ መሪዎች ተወካይ፣ የሃይማኖት መሪዎች ተወካይ፣ የሲቪክ ማህበራት ም/ቤት ተወካይ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ተወካይ፣ የወረዳ አስተዳደር ተወካይ፣ የሸሪያ ፍርድ ቤት ዳኞች (ቃዲዎች)፣ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች እና የሀገር ሽማግሌዎች (ሱልጣኔቶች) በክልሉ የኮሚሽኑ ተባባሪ አካላት ሆነው ይሰራሉ፡፡

በኮሚሽኑ አዘጋጅነት እየተሰጠ የሚገኘው ስልጠና ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን ሰልጣኝ ተባባሪ አካላቱ ስለ ምክክር መሰረታዊ ፅንሰ ሀሳቦች፣ ስለ ኮሚሽኑ ዓላማ እና መርሆች እንዲሁም በተሳታፊዎች ልየታ ሂደት ላይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ግንዛቤን ለመፍጠር ታስቦ እየተካሄደ ይገኛል፡፡