የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ በምክክር ምዕራፍ ላይ ተሳታፊ ለሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ገለፃ አድርጓል፡፡
ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የምክክር ምዕራፍን በይፋ ያስጀመረው ኮሚሽኑ ዛሬ ግንቦት 23 ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለተውጣጡ ወኪሎች በአደዋ ሙዚየም አዳራሽ ስለ ምክክር ምዕራፉ ገለፃ እና ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
በዕለቱ በተዘጋጀው የገለፃ መርሃ-ግብር የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ማህበራት ተወካዮች ፣ የሶስቱ የመንግስት አካላት ተወካዮች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን የወከሉ ተሳታፊዎች ተካፍለዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፋን አርአያ (ፕ/ር) በቀጣይ ቀናት በሚደረገው የምክክር ምዕራፍ መርሃ-ግብር ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል::
በሌላ በኩል የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ለተሰብሳቢዎች በአጀንዳ አሰባሰብ ሂደቶች ላይ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘውን የምክክር ምዕራፍ ጨምሮ በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በከተማ አስተዳደር ደረጃ የሚካሄደው ምክክር እነዚህ ባለድርሻ አካላትና ከየሕብረተሰብ ክፍሉ ወኪሎች የተመረጡ ተሳታፊዎች በጋራ በሚገኙበት በነገው ዕለት በሚኖር የማስጀመሪያ ስነስርዓት የሚጀመር ይሆናል፡፡
በቀጣዮቹ ቀናት እነዚህ አካላት በጋራ በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን እንደሚያደራጁ ይጠበቃል፡፡