የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ሀገራዊ ምክክር

ሀገራዊ ምክክር ምንድነው?

ሀገራዊ ምክክር በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሀሳብ ልዩነቶች ሲፈጠሩ፣ በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት፣ ከጦርነት በኋላ በተከሰቱ ሁኔታዎች ወይም ሰፊ የፖለቲካ ሽግግሮች ውስጥ ባሉ በርካታ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባት ለመፍጠር የታለመ በሀገራዊ ባለቤትነት የተያዘ ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ ያለው የምክክር ሂደት ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በበኩሉ ሀገራዊ ምክክር ማለት በአዋጁና የኮሚሽነሮች ምክር ቤት በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በሚለዩ አጀንዳዎች ላይ በተለያዩ አካላት ውይይት እንዲደረግባቸው የኮሚሽኑ ምክር ቤት በፌደራልና በክልሎች የሚያመቻቸው ውይይቶች እንደሆኑ አብራርቷል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ፋይዳው ምንድነው?

ሀገራዊ ምክክሮች እንደየሀገቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች የተለያዩ ዓላማዎችን ለማሳካት ሊከናወኑ ይችላሉ፡፡ ከነዚህም መካከል፡-

  • በአንድ ሀገር የተከሰቱ ከባድ የፖለቲካ ችግሮችን ወይም በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ መሠረታዊና ለሀገር ህልውና አስጊ የሆኑ ልዩነቶችን ለመፍታት፤
  • ልዩነቶችን/አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፤
  • በመንግስትና በሕዝብ መካከል መተማመንን ለማስፈን፣
  • ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማጠናከርና ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባህል እንዲዳብር ለማድረግ፤
  • ሀገራዊ ምክክሮችን በማድረግ የአዲስ (ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ) ያደገና የተለወጠ ሥርዓት ባለቤት ለመሆንና በዜጎች መካከል የተሻሻለ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር፤ እንዲሁም
  • ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ጉልህ ፋይዳ አላቸው፡፡

የዓለም ተሞክሮ ስለ ሀገራዊ ምክክር ምን ይነግረናል?

ሀገራዊ ምክክር ለዓለማችን አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ የሀገራዊ ምክክሮች ታሪክ በአብዛኛው በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ከተስተናገዱ ምክክሮች ጋር ተዛምዶ ሊታይ ይችላል፡፡

 

 the first

የመጀመሪያው የኮሙኒዝም ስርዓት በምስራቅና መካከለኛው አውሮፓ መንኮታኮት ጋር ይያያዛል፡፡ በ1989 (እ.አ.አ) በነዚህ ሀገራት የኮሙዩኒዝም መፈራረስ ያስከተለውን ዋና ዋና የፖለቲካ ስንጣቃቶችን ለመቋቋም ፖላንድ፣ ሃንጋሪ፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ምስራቅ ጀርመን እና ቡልጋሪያ በተከታታይ ጠረጴዛ ስበው ለምክክር ተቀምጠዋል፡፡

 the second

 

ሁለተኛው የሀገራዊ ምክክር ማዕበል በአፍሪካ ውስጥ በዜጎች እና ሥልጣን በያዙ መሪዎች መካከል እያደገ በመጣው ልዩነት፣በርካታ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ (ፍራንኮፎን-አፍሪካ) ሀገራት በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሀገራዊ ምክክር እንዲያደርጉ በሆኑበት መነጽር ውስጥ የሚታይ ነው።

 

the third

ሦስተኛው በ1990ዎቹ ብዙ አገራት በላቲን/በደቡብ አሜሪካ ውስጥ አሳታፊ አስተዳደርን ለመመስረትና ልማትን ለማጠናከር መግባባት ላይ የተመሰረቱ የሕገ መንግሥት አወጣጥ ሂደቶችን በተከተሉበት ወቅት የሀገራዊ ምክክር ሂደትን በስፋት ከመጠቀማቸው ጋር በተያያዘ ሊታይ የሚችል ነው። ከዚህ አኳያ እንደ ቦሊቪያ እና ኮሎምቢያ ያሉ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት በሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት የተደረሰባቸው ሂደቶች የሀገራዊ ምክክሮች ቁልፍ ገጽታዎች የተንጸባረቁባቸው ናቸው።

 the forth

 

አራተኛው የቅርቡ በመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ ሀገራት ከተቀጣጠለው የአረብ አብዮት ጋር በተያያዘ ጎልቶ የታየው ምክክር ነው፡፡ አብዮቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአንዱ አገር ወደ ሌላ አገር በመስፋፋቱ ሀገራዊ ምክክሮች (ወይም ተመሳሳይ ሂደቶች) በሞሮኮ፣ ሊቢያ፣ ቱኒዚያ፣ ግብፅ ተካሂደዋል። በተጨማሪ ሱዳን፣ ሊባኖስ፣ ዮርዳኖስ፣ ባህሬን እና የመንም ሀገራዊ ምክክሮችን ያስተናገዱ ሲሆን በስኬትም በውድቀትም ማሳያ የሆኑ ሂደቶችን አልፈዋል፡፡  

የሂደቱ ዝርዝር፣ ያገጣሟቸው ፈተናዎችና ያስገኟቸው ውጤቶች የተለያዩና በሰፊው ሊታዩ የሚችሉ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለጊዜው በሂደቶች ውስጥ በወል የታዩና ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚችሉ ጉዳዮችን መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

  • ውስብስብ የለውጥ ሂደቶችን ለመቆጣጠር ምክክርን እንደ መሳሪያ መጠቀማቸው፤
  • ሰፋ ባለ መልኩ ባለድርሻ አካላትን ያካተቱ መሆናቸው፤ እንዲሁም
  • ምንም እንኳን በእያንዳንዱ ሀገር የነበረው ሂደት ለተለያዩ ተግዳሮቶች ምላሽ የሰጠ ቢሆንም በአብዛኛው በተለምዶ በሀገር ጉዳይ ላይ ውስን ሊሂቃን ብቻ ከሚያደርጉት ውይይትና ስምምነት ወጥቶ ከነ ውስንነቱ ሰፊውን የህበረተሰብ ክፍል በማካተት ወደ አሳታፊ ፖለቲካ ለመሸጋገር ጥረት የተደረገባቸው መሆናቸው ተጠቃሽ ናቸው ።




ሀገራዊ ምክክር በተለያዩ ሀገራት

ካሜሩን

cameroon

የመን

yemen

ቱኒዚያ

tunisia

ግብጽ

egypt

dialogue
 

ሀገራዊ ምክክሮች የተለያዩ ዓላማዎችን ለማሳካት ይካሄዳሉ፡፡ ዓላማቸውን መሰረት በማድረግም በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡

ሀ.   የአጭር ጊዜ ግብን ለማሳካት የሚካሄድ ሀገራዊ ምክክር

ይህ ዓይነቱ ምክክር የሚደረገው በዋናነት ቀውስን ለመከላከልና የተፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት ታስቦ ነው፡፡ ምክክሩ በአጭር ጊዜ፣ በውስን ጥረትና የሚመለከታቸውን ሀይሎች ብቻ በማሳተፍ የሚካሄድ ሲሆን ሊፈጠር የሚችል ቀውስንና ግጭትን ለመከላከለል ወይም የተፈጠረን ቀውስ ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ የሚውል የምክክር ዓይነት ነው፡፡ ስልታዊ በሆነ መንገድ የሚከናወን ሲሆን የፖለቲካ ውዝግቦችን በመፍታት መለስተኛ የሆነ መግባባትን እንደገና ለመፍጠር ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

  የአጭር ጊዜ ግብ ያለው ሀገራዊ ምክክር መገለጫዎች

  • ጥቂት ተልዕኮዎች ብቻ ይኖሩታል፤
  • አነስተኛ ስፋት እና አጭር ቆይታ ይኖረዋል፤
  • በምክክሩ የሚሳተፉት አካላት ውስን ቁጥር ያላቸው በመሆናቸው የምክክር ሂደቱን ለማከናወን ይቀላል፤
  • ሰፊ መሰረት ያለው እና አካታች የሆነ ምክክርን የግድ አይጠይቅም፡፡

      ለ.  መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ሀገራዊ ምክክር

ይህ ዓይነቱ ምክክር በባህሪው ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ፣ ሰፊ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ፣ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያካትት፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ባሉ መሰረታዊ ልዩነቶች ላይ በማተኮር ልዩነቶቹን ለማጥበብ የሚደረግ ምክክር ነው፡፡ በውጤቱም የመንግሥትና ማኅበረሰብ ግንኙነቶችን እንደገና ለመወሰን ወይም አዲስ ማህበራዊ ውል ለመመሥረት የሚያስችል አቅም ያለው ሲሆን ሀገርን ወደ አዲስ የዲሞክራሲና ልዩነቶችን ከሀይል አማራጭ ይልቅ በመመካከር የመፍታት ባህል ለማሸጋገር መሰረት የሚጥል የምክክር ዓይነት ነው፡፡

አንዳንድ ሀገራዊ ምክክሮች ሁለቱንም ያጣመረ ዓላማ ይዘው የአጭር ጊዜ ችግሮችን ለመፍታትና ለአለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ይካሄዳሉ፡፡

 በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው የምክክር ዓይነት ሁለቱንም ዓላማዎች የያዘ መሆኑን በሚከተለው መልኩ ከተገለጹት የምክክር ኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ በግልጽ ለመረዳት ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ የሚካሄዱት ሀገራዊ ምክክሮች

በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት የማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት የመፍጠርለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላድል ለመፍጠር፣ ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ተፈተው አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካ እና የማህበራዊ መደላድል ለማመቻቸት እንዲሁም ለአገራዊ መግባባት እና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ጽኑ መሠረትመጣል እንዲሁም ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ተፈተው አስተማማኝ ሰላም የሚረጋገጥበትን የፖለቲካ እና የማኅበራዊ መደላደል ለማመቻቸት

ሲባል የሚከናወን መሆኑን በአዋጁ በግልጽ ተመላክቷል፡፡ 

/የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 6/

ወቅታዊ ችግሮችን መፍታትና የረጅም ጊዜ ግብን መሰረት ያደረጉ ሀገራዊ ምክክር መገለጫዎች

  • ሰፊ ተልዕኮዎች፣ተግባራትና ሀላፊነቶች ይኖሩታል፤
  • በአብዛኛው ሰፊ መሰረት ኖሮት ይከናወናል፤
  • የተለያየ ጥቅም እና ፍላጎት ያላቸውን ሰፊ የማህበረሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ከፍ ያለ ተቀባይነትን ማግኘት ይጠይቃል፤
  • ውጤት ላይ ለመድረስ በተራዘመ ጊዜ በርካታ ሂደቶችን ማለፍን ይጠይቃል ፤
  • በፍጥነት ወደ ውጤት የማይኬድበት በመሆኑ የባለድርሻ አካላትን ትዕግስት ይፈታተናል፤
  • ምክክር የሚደረግባቸው ጉዳዮች ወቅታዊ  እና ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡

 

ምክክር ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ወይም ግጭቶችን ለማስወገድ ጥቀም ላይ ከሚውሉ አማራጮች መካከል አንዱ እንጂ ብቸኛው አማራጭ አይደለም፡፡ ከሚታወቁት ሰላማዊ የልዩነት ወይም የግጭት መፍቻ መንገዶች መካከል ውይይት፣ እርቅ፣ ድርድር ወይም ክርክር ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ምክክር፡ ውይይት፣ ክርክር፣ እርቅ ወይም ድርድር ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ያላቸውን ተቀራራቢነት በመውሰድ አንድና ተመሳሳይ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌዎች በስፋት ይታያሉ፡፡ በመሆኑም ለግንዛቤ እንዲረዳ ከምክክር አኳያ ያላቸውን ልዩነት በአጭሩ መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ሀ. ድርድር (Negotiation)

ተቀናቃኝ ኃይሎች በቀጥታ የሚሳተፉበት ሂደት ሲሆን ካለ ሶስተኛ ወገን አስማሚነት ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚደረገው ጥረት የውሳኔ ሃሳቦችን የሚያፈልቁበት ሂደት ነው። በሂደቱ ለድርድር የሚቀመጡት ወገኖች ተቀባይነት ያለው ታዛቢ ይሰይማሉ፡፡ በድርድሩ ወቅት አንዱ አካል ከሌሎች ተደራዳሪዎች ልቆ ለመውጣት ይጥራል፡፡

ለ. ሽምግልና (Mediation)

ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች በፈቃዳቸው ተቀባይነት ባለው ሶስተኛ ወገን (አሸማጋይ/ሽማግሌ) አማካይነት በመካከላቸው የተፈጠሩ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚደረግ የግጭት ወይም የአለመግባባት መፍቻ አንድ መንገድ ነው፡፡ የግጭቱ ወይም የልዩነቱ ዋና ባለድርሻ አካላትን የሚያካትት ሲሆን የሌሎች ባለድርሻ አካላትን አስተያየት እና ፍላጎቶች በተለያዩ የተሳትፎ መንገዶች ወደ ሂደቱ እንዲቀላቀሉ ያደርጋል። ባለድርሻ አካላቱ ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ካልቻሉ የመሸምገል ወይም የማስታረቅ ሚና ያለው ወገን ለማስማማት የመወሰን አቅም የለውም፡፡ ነገር ግን ያስማማሉ የሚላቸውን ነገሮች/ሃሳቦች ማቅረብ ይችላል፡፡

ሐ. ክርክር/ሙግት (Argument)

የሀሳብ ፉክክር ነው፡፡ የሚደግፉት ሀሳብና አቋም አሸናፊ እንዲሆን ማድረግ ላይ ያተኩራል፡፡ ሌሎች የሚያራምዱት ሀሳብ አመክንዮ “ስህተት” መሆኑን ለማስረዳትና ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋል፡፡ የሌሎችን ድክመቶች በመፈለግ አቋማቸውን ይተቻል፡፡ የመደማመጡ ግብ የሌላውን ወገን ሀሳብ ለመረዳት ሳይሆን ድክመትን በመፈለግ ለመተቸት ነው፡፡ በግጭት እና ልዩነት ላይ ማተኮርን እንደ ልዩ ጥቅም ይመለከታል፡፡ ለጋራ የሆኑ ጉዳዮችና ለመልካም ግንኙነቶች ቦታና ዋጋ አይሰጥም፡፡

መ. ውይይት (Discussion)

ፅንሰ-ሀሳቦች ላይ በመነጋገር ያተኩራል፡፡መረጃንና እውቀትን የማካፈል ዓላማ አለው፡፡ በማጠቃለያው ላይ “ገለልተኛ” ሆኖ የመቆየት/ የመታየት አዝማሚያ ይታይበታል፡፡ ለተነሱ ጉዳዮች መፍትሄና ምላሽ ለማፈላለግ ጥረት ያደርጋል፡፡ ግጭት እና ልዩነት ሊፈጥሩ ወይም ሊያባብሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማስወገድ ጥረት ያደርጋል፡፡ ከክርክር በተለየ መልኩ ለጋራ ጉዳዮችና መልካም ግንኙነቶች ዋጋ ይሰጣል፡፡

ሠ. የግልግል ዳኝነት (Arbitration)

ተቀናቀኝ ኃይሎች/አካላት ችግራቸውን ለግልግል ዳኞች በማቅረብ ውሳኔ የሚያገኙበት መንገድ ነው፡፡ ችግራቸው ለዳኞች የሚቀርበው በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የጋራ የሆነ ስምምነት ሲኖር ነው፡፡ ተቀናቃኝ ኃይሎች በጋራ ባደረጉት ስምምነት ፍርድ የሚሰጧቸውን ዳኞች ይመርጣሉ ፡፡ የግልግል ዳኞች በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል ውሳኔ የማሳለፍ ሙሉ ስልጣን አላቸው ፡፡

 

ረ. ምክክር (Dialogue)

በአንድ ሀገር ውስጥ በመሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊና ስር የሰደዱ ልዩነቶች ሲያጋጥሙ በበርካታ ሀገራዊ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባት ለመፍጠር ያለመ ሂደት ነው፡፡  

የሀገራዊ የምክክር መድረኮች በአመለካከት፣ በእምነት፣ በብሄር፣ በእድሜ፣ በጾታ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲሁም የፖለቲካ መሪዎቸን በማገናኘትና በልዩነቶቻቸው ዙሪያ እንዲመካከሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ሁነኛ መሳሪያ ነው።

ሀገራዊ ምክክር እንደ ክርክር የኔ ሀሳብ ወይም አቋም ትክክል ነው በሚል የሌላውን ሀሳብ ወይም አቋም በማጣጣልና በመድፈቅ የራስን ሀሳብ የበላይነት ለማሳመንና ለማንገስ ጥረት የሚደረግበት አይደለም፡፡ እንደ ድርድርም በሰጥቶ መቀበል መርህ በጉዳዮች ላይ ተስማምቶና ለተግባራዊነቱ አሳሪ ህጎችን በማውጣት የሚተገበር አይደለም፡፡

ምክክር እንደ ውይይትም በጉዳዮች ላይ ተወያይቶና መረጃ ተለዋውጦ መለያየት አይደለም፡፡ ይልቁንም በመደማመጥ፣ አንዱ የሌላውን አቋምና እውነት ለመረዳት ጥረት በማድረግ ወይም አንዱ በሌላው ጫማ ውስጥ ሆኖ በማሰብ ለህዝብና ለሀገር የሚበጅ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚደረግ አሳታፊ፣ አካታች፣ የአብዛኛው ማህበረሰብ ጉዳዮች በሆኑ አጀንዳዎች ላይ የሚያተኩር፣ ግልጽ የሆነ አካሄድና ገለልተኛ የሆነ አመቻችን የሚጠይቅ ሂደት ነው፡፡

በአብዛኛው የሀገራዊ ምክክር ባለቤትም ሆነ ዋነኛ ፈጻሚ ሰፊው ህዝብ መሆኑ ከሌሎች ግለሰቦች ወይም ውስን ቡድኖች ከሚገኙባቸው የልዩነት ወይም የግጭት መፍቻ መንገዶች የተለየ ያደርገዋል፡፡ የውጭም ሆኑ የአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት ለምክክሩ የተሳካ መሆን አስቻይ (ምቹ) ሁኔታዎችን ከመፍጠር በዘለለም ውጤቱ ላይ ተጽእኖ እንዲፈጥሩ አይፈቅድም፡፡ 

በምክክርና ሌሎች የግጭት መፍቻ መንገዶች ጽንሰ ሀሳቦች ዙሪያ የተገለጹት ልዩነቶች ቢኖሩም በአተገባበር ግን ዘላቂ መፍትሄዎችን ለማስገኘት ሲባል በጥምረት ጥቅም ላይ ሲውሉ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ የተካረሩ ልዩነቶችን ወይም ደም አፋሳሽ ግጭቶችን በቅድሚያ በድርድር ወይም በሽምግልና በመፍታት መሰረታዊ ልዩነቶችን በሀገራዊ ምክክር ዘላቂ መፍትሄ ወደ ማስገኘት ማሸጋገር ይቻላል፡፡

ሀገራዊ ምክክሮች እንደሌሎቹ ውጤት ላይ ብቻ ሳይሆን በሂደቱ ላይ ጭምር የሚያተኩሩና ለሂደቱ አካታችነት፣ አሳታፊነት፣ ግልጽነትና ፍትሀዊነት ትኩረትና ላቅ ያለ ዋጋ የሚሰጡ ናቸው። ከሚያስገኙት ውጤት እኩል ወይም በበለጠ ሁኔታ የሂደታቸው ቅቡልነት፣ አካታችነትና ተዓማኒነት ወሳኝ ነው፡፡

ይህ ሲባል ሀገራዊ ምክክሮች ተጨባጭ ውጤቶች የሏቸውም ማለት አይደለም፡፡ በተጨባጭ የሚያስገኟቸው ውጤቶች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ እነዚህ ውጤቶች የተገኙባቸው ሂደቶች ግን መለያ ባህሪያቸው ናቸው። በሌላ አነጋገር ሀገራዊ ምክክሮች ዘላቂ መግባባት እና መተማመንን ለመፍጠር ሂደትን ማዕከል ያደረጉ መድረኮች ናቸው ማለት ነው።

ሂደቱን በጥንቃቄ በማለፍ ውጤታማ መሆን ግን በቀላሉ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በማህበረሰቡ የተለመዱ፣ በብቸኝነት ትክክል መስለው ለዘመናት የኖሩ ወይም ለፖለቲካና ለልዩ ልዩ ጥቅም ሲባል እንዳይነኩ የሚፈለጉ ነባር አውዶችንና አመለካከቶችን ሊነካ የሚችል በመሆኑ ከተለምዷዊ አውዱ ጋር ፊት ለፊት መገናኘትን ወይም መጋጨትን፣ ለዘመናት የቆዩ ቁስሎችን መነካካት ይጠይቃል፡፡ ይህም ከልዩነት ይልቅ የሚያግባቡ ጉዳዮችን ሊያጠናክር ወይም ልዩነቶቹ ይበልጥ እንዲከሩና አለመግባባቱ ጎልቶ እንዲወጣ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ሀገራዊ ምክክሮች ሰፊ መሰረት ያላቸውና አሳታፊ ሂደቶች በመሆናቸው ለበለጠ የትብብር ተሳትፎ እና መከባበር መሠረት የመጣል ሰፊ እድልና አቅም አላቸው፡፡

አንድ ሀገራዊ ምክክር አሳታፊና አካታች ነው ለመባል ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው አህዛዊ መግባባቶች ወይም ወሰኖች የሉም፡፡ ይሁንና ምክክር እንደየሚደረግባቸው አጀንዳዎች ስፋትና ጥልቀት የተሳታፊዎች ብዛትና ተካታችነት ውስን፣ መካከለኛ ወይም ብዛት ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ሀገራዊ ምክክሩ አስፈላጊ የሆነበትን ውጤት ለማስገኘት ግን የአሳታፊነትና የአካታችንትን ሚዛን መጠበቅ እንዲሁም ወሳኝ የሆኑ አጀንዳዎች ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ማድረግ መሠረታዊ መስፈርቶች ናቸው፡፡ አካታች ሆኖ የማያሳትፍ፣ ወይም አሳታፊ ሆኖ አካታች ያልሆነ ወይም መሰረታዊ አጀንዳዎችን በጥልቀት ወደ ምክክር መድረኩ የማያመጣ ወይም የሀሳብ ልዩነት ያላቸውን ወገኖች ፊት ለፊት የማያገናኝ ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ መሆን እንደማይችል ሰፊ መግባባት አለ፡፡

inclusive


ሀገራዊ ምክክር በምን ያህል መጠን አካታችና አሳታፊ ይሁን ወይም የትኞቹ አጀንዳዎች ላይ ምክክር ይደረግ የሚሉ ጉዳዮችን ለመወሰን የቀደመ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት የተለያዩ አካሄዶችን ተከትለዋል፡፡ አንዳንዶቹ የምክክር ሂደቱን ለመምራትና ለማከናወን ባወጧቸው አዋጆች/ህጎች በግልጽ አስቀምጠው ለመተግበር የሞከሩ ሲሆን አንዳንዶቹም ይህን የመወሰን መብቱን ሀገራዊ ምክክሩን እንዲመራ ለሰየሙት ተቋም ወይም አካል ሰጥተው የሂደቱ አንድ አካል አድርገዋል፡፡በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የመረጠቸው አካሄድ ተጠቃሽ ነው፡፡ የምክክር ሂደቱን በበላይነት እንዲመራ ለተቋቋመው ኮሚሽን መሠረታዊ መርሆችን በማስቀመጥ ብቻ እነዚህን ዝርዝር ተግባራት እንዲወስን ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ይህ መሆኑ በራሱ ኮሚሽኑ በአጠረ ጊዜ ውስጥ እንዲያከናውን ከሚጠበቅበት በርካታ ተግባራትና ሀላፊነቶች አኳያና ከሀገራዊ ምክክር ሂደት ባህርይ አኳያ ጫና የሚፈጥር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሰፊው ህዝብ በተለያየ ደረጃ እንዲሳተፍ እንዲሁም የምክክር አጀንዳዎቹን በራሱ እንዲሰጥና በስፋትም እንዲመክርባቸው በማድረግ መሰረቱ ሰፊና ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ውጤት ለማስገኝት እድል የሚሰጥ ነው፡፡

ሀገራዊ ምክክርን በተመለከተ ዓለም እስካሁን ካለፈችባቸው ሂደቶች የተቀመረና ወጥ የሆነ አካሄድ ወይም ፎርሙላ የለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ መሠረታዊ መርሆዎች ላይ መግባባት አለ፡፡ ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ሀ. ሕዝባዊ ተቀባይነት

የምክክሩ አስፈላጊነትና የውጤቱ ተጠባቂነት በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ሊኖረው ይገባል፡፡

ለ. የመንግስት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት

መንግስት በቅድሚያ መግባባት ሊፈጠርባቸው የሚገቡ ልዩነቶች መኖራቸውን ከመቀበል ጀምሮ ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት እንዲቻል የፖለቲካ ተነሳሽነቱን መውሰድ እንዲሁም ለሂደቱ መሳካትና ለምክረ ሀሳቦቹ ተፈጻሚነት ከፍተኛና የማያቋርጥ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ሐ. አካታችነት

ይህ የተለያየ አመለካከት ያላቸውን፣ በተለያየ ጾታ፣ የእድሜ ክልል እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በበቂ መጠን ማሳተፍና በፍትሀዊነትና በዕኩልነት የመመልከት መርህ ነው፡፡ አካታችነት በሁሉም የምክክር ሂደቶችና ተግባራት ላይ ሊንጸባረቅ የሚገባው መርህ ነው፡፡

መ. አሳታፊነት

የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች /constituencies/ በንቃትና ገንቢ በሆነ ሁኔታ እንዲሳተፉ የማድረግ መርህ ነው፡፡ ስለምክክር ምንነትና ፋይዳ እንዲሁም ሂደቶችና ተሳትፎ ግንዛቤ በመፍጠርና አቅምን በመገንባት ትርጉም ያለውና ሙሉ ተሳትፎን የሚያረጋገጥ የምክክር ሂደት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

ሰ. ግልጽነት

የሚከናወኑ ተግባራትና የሚከናወኑበት ሁኔታ ግልጽና ሌሎች በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት መሆኑን የማረጋገጥ መርህ ነው፡፡ ከዚህ መርህ አኳያ ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን የተለያዩ የአሰራር ሥርዓቶችን በማዘጋጀትና በመተግበር እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በዝግጅት ሂደት ላይ ጭምር በማሳተፍ ግልጽነት መፍጠር ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

ረ. ተአማኒነት

በምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎችና ፈጻሚዎች እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ አመኔታና ከፍ ያለ ተቀባይነት የማግኘት መርህ ነው፡፡ በተለይ ሀገራዊ ምክክር ሂደቱና ውጤቱን በተመለከተ የተለያዩ አካላት ፍላጎት ጎልቶ የሚንጸባረቅበትና በጥርጣሬዎች የታጀበ በመሆኑ ተአማኒነትን ለማግኘት ከፍ ያለ ጥረትን ይጠይቃል፡፡

ሰ. ገለልተኝነት

ለየትኛውም ሀሳብ፣ አመለካከት ወይም አቋም የተለየ ድጋፍ ወይም እገዛ ያለማድረግ ወይም በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ይህን የሚያንጸባርቅ ሁኔታ ያለማሳየት መርህ ነው፡፡ በዚህም ረገድ በተለይም የምክክር ሂደቱን የሚመሩ አካላትን ገለልተኝነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ ሰዎችን ከመምረጥ ጀምሮ ተግባሮቻቸውን የሚያከናውኑባቸውን የአሰራር መመሪያዎችንና የስነምግባር ውስጠ ደንቦችን ማዘጋጀትና በጥብቅ ክትትል ተፈጻሚ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሸ. ተግባራዊነት

በምክክር ሂደቱ የሚደረስባቸው መግባባቶች በሂደት እንዲፈጸሙ የማድረግ መርህ ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክር ትልቅ የሽግግር ፍኖተ ካርታ አካል ሆኖ በኢኮኖሚ፣ በመዋቅራዊ፣ በፖለቲካ እና በፍትህ ማሻሻያ ሂደቶች መታጀብ አለበት። ሀገራዊ ምክክሮች በራሳቸው ፍጻሜ ሳይሆኑ የተቀናጀና አሳታፊ የለውጥ ሂደት ጅምር መሆናቸው መታወቅ አለበት።