የአማራ ክልል የምክክር ሂደት በብዙ መልኩ ታሪካዊ ነው- ኮሚሽኑ
ሚያዚያ 4/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ ሲያካሂደው የነበረው የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ ሚያዚያ 4/2017 ዓ.ም ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡
የተመረጡ የባለድርሻ አካላት ወኪሎች ያጠናቀሯውን አጀንዳዎች የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያምና ኮሚሽር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በጋራ ተረክበዋል፡፡
የምክክር ሂደቱ መጠናቀቁን በማስመልከት መልዕክት ያስተላለፉት ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም የሀገራዊ ምክክር ሂደት እንደ ሀገር ታሪካዊ ሂደት መሆኑን ጠቁመው የአማራ ክልል ደግሞ ብዙ ውጣውረዶችን በማለፍ የተሳካ በመሆኑ ለኮሚሽኑ ተጨማሪ ታሪካዊ ክስተት ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ምክክር ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ የለም በሚል ገና ከጅምሩ ብዙዎች አይሳካላቸውም በማለት ሲተቹን ነበር፣ ነገር ግን ወደ ክልሉ ከገባን ጀምሮ የክልሉ ህዝብ ከጎናችን ሆኖ ለዚህ ታሪካዊ ስኬት አብቅቶናል ብለዋል ኮሚሽነሩ በመልዕክታቸው፡፡ ለዚህም መላ የክልሉን ህዝብ በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ገለፃ የክልሉ የምክክር ተሳታፊዎች ከክልላቸው አልፈው ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ጉልህ ሚና ያላቸውን አጀንዳዎች ለይተው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
የአማራ ክልል አጀንዳዎች ወደ ኮሚሽኑ ምክር ቤት ቀርበው ከሌሎች ክልሎች አጀንዳዎች ጋር ተጠምረው እንደሚቀረፁ ኮሚሽነር መላኩ አረጋግጠዋል፡፡
የቀረቡ አጀንዳዎች ተፈፃሚ ይሆኑ ዘንድ የክልሉ ህዝብ ከኮሚሽኑ ጎን በመሆን የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲያደርግም ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከመጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ሚያዚያ 4/2017 ዓ.ም ድረስ በሁለት ምዕራፎች ሲካሄድ በነበረው የአማራ ክልል የምክክር መድረክ ከ6ሺ በላይ ወኪሎች ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡
ለምክክሩ መሳካት ሚና ለነበራቸው ሁሉ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሂደቱን የኮሚሽኑ ኮሚሽሮች ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያምና ኮሚሽነር ዮናስ አዳዮ (ዶ/ር) በበላይነት የመሩት ሲሆን በርካታ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ለሳምንታት ባህርዳር ከተማ ከትመው ከሌሎች ተባባሪ አከላት ጋር በጋራ ለስኬት አብቅተውታል፡፡