የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ነገ ይጀምራል

fb img 1743766074262

የአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ነገ ይጀምራል

መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (ባህርዳር)

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ከነገ መጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ በባህርዳር ከተማ እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያምና ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) መርሃግብሩን በተመለከተ በባህርዳር ከተማ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

መግለጫውን በፅሁፍ ያቀረቡት ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ኮሚሽኑ በአማራ ክልል የተሳታፊ ልየታ መርሃ-ግብሩን አጠናቆ በሙሉ አቅሙ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ መሸጋገሩን አስታውቀዋል።

በመድረኩ ከክልሉ ወረዳዎች አስር የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው የተመረጡ ከ4ሺህ 500 በላይ የህብረተሰብ ወኪሎች ከነገ መጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምረው ለተከታታይ አራት ቀናት የአጀንዳ ሃሳቦቻቸውን በውይይት እንደሚያጠናቅሩም አክለዋል፡፡

በዚህ የምክክር ሂደት ሁለተኛ ምዕራፍ የተመረጡ የወረዳ ማህበረሰብ ክፍል ወኪሎችን ጨምሮ የመንግሰት ፣ የተቋማትና ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወኪሎች አጀንዳዎቻቸውን በውይይት አዳብረው በማጠናቀር ለኮሚሽኑ እንደሚያስረክቡም ተመላክቷል፡፡

ከነገ መጋት 27 እስከ ሚያዚያ 4/2017 ዓ.ም በሚቆየው የአማራ ክልል የምክክር መድረክ ከአምስቱ የምክክር ባለድርሻ አካላት በጥቅሉ ከ6ሺህ በላይ ወኪሎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

ይህ የምክክር ምህራፍ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው አጀንዳዎች የሚሰበሰቡበት መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በንቃት በመሳተፍ የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን እንዲሰጡ በኮሚሽኑ ስም ጥሪ አቅርበዋል።

ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ኮሚሽር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) በበኩላቸው በአማራ ክልል የሚካሄደው ምክክር አካታችና አሳታፊ እንዲሆን በተደረገው ጥረት የክልሉን ባለድርሻ አካላት የማሳተፍ ስራ መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡

ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ቢሆኑም ካሉበት ቦታ ሆነው አጀንዳዎቻቸውን ቢልኩ ኮሚሽኑ ለመቀበል አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን አንስተዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ በተሳታፊ ልየታ መርሃግብሮች ሀገራዊ እና ክልላዊ ፋይዳ ያላቸውን ሃሳቦች ሲያንሸራሽ ታዝበናል ያሉት ኮሚሽር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ይህ ሁኔታ ተሳታፊዎች ነፃና አካታች በሆነ መልኩ መለየታቸውን የሚያረጋግጥ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ምክክር ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መኖሩ ተረጋግጦልን ስራችንን እያከናወንን ነው ሲሉ ከጋዜጠኖች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ደግሞ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ናቸው፡፡

መገዳደል መፍትሄ አይደለም ያሉት ኮሚሽነር መላኩ የምክክሩን ሂደት ተጨባጭ ባልሆነ ሁኔታ ከመተቸትና ራስን ከማግለል ሁሉም አካል አጀንዳውን ይዞ ወደ ምክክሩ እንዲመጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡