የፌዴራል ባለድርሻ አካላትን በአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ማሳተፍ ለምን አስፈለገ?
የካቲት 18/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 በተሰጠው ስልጣን እና ሀላፊነት መሰረት የምክክር አጀንዳዎችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በህዝባዊ ውይይቶች እና ሌሎች አግባብነት ባላቸው መንገዶች እየሰበሰበ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
ኮሚሽኑ ይህንን ቁልፍ የምክክር ምዕራፍ ሲተገብር በክልል፣ በፌዴራል እና በዲያስፖራው ማህበረሰብ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ከግምት በማስገባት እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ጉዞው በክልል የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍን የተገበረ ሲሆን የፌዴራል ባለድርሻ አካላትም በሂደቱ የሚሳተፉበትን መድረክ በቅርቡ ለማዘጋጀት እየተሰናዳ ይገኛል፡፡
ለመሆኑ በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን በዚህ ሂደት ማሳተፍ ለምን አስፈለገ? ከዚህ ቀጥሎ ያሉ ሀሳቦች ይህንን ጥያቄ ያብራራሉ፡፡
- ሀገር አቀፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለማድረግ
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ የፌዴራል ባለድርሻ አካላት እንደሀገር ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገባቸውን የፖሊሲ ጉዳዮች ነቅሰው በመለየት በአጀንዳነት የማንሳት ዕድል አላቸው፡፡ እነዚህ አካላት በመዋቅራዊ ቁመናቸው በፖለሲ ደረጃ ሊገለፁ የሚችሉ ጉዳዮችን የሚሰሩ በመሆናቸው በዚህ ሂደት መሳተፋቸው ጠቃሚ እንደሆነ ይታመናል፡፡
- በሁለትና ከዚያ በላይ ክልሎች መካከል ያሉ ጉዳዮችን ለማስተናገድ
የፌዴራል ባለድርሻ አካላት በተሰጣቸው አስተዳደራዊ መዋቅር መሰረት በተለያዩ ክልሎች መካከል የሚነሱ የጋራ ጉዳዮችን ያስተናግዳሉ፡፡ ሂደቱ በሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች ውስጥ የሚከሰቱ የድንበር፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የፀጥታ ጉዳዮችን፣ ወዘተ በተመለከተ በፌዴራል ባለድርሻ አካላት በአጀንዳነት ሊቀርቡ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ይረዳል፡፡
- አካታችነትን ለማስፈን
በፌዴራል የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ በንቃት መሳተፋቸው ኮሚሽኑ በሁሉም ደረጃ የሚገኘውን የአስተዳደር መዋቅር ማካተቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ሂደቱ በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው የጋራ በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ገንቢ ውይይቶችን እንዲያደርጉ መንገዱን ከማመቻቸቱም በላይ የምክክሩ ውጤትም ተግባራዊ እንዲሆን በጎ ሚና እንዲጫወቱ ያግዛል፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!