የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አስጀምሯል።
በአደዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ በተጀመረው የምክክር ምዕራፍ የህብረተሰብ ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ፣ የሶስቱ የመንግስት አካላት ማለትም ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ ፣ የተቋማትና የማህበራት ተወካዮች እንዲሁም የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
በምክክር ማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) አካታችና አሳታፊ ወደሆነው የዝግጅት ምዕራፍ ማገባደጃ እንዲሁም የምክክር ሂደት መግቢያ እና አጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ማብሰሪያ ሂደት እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ፈተናዎቹ ሳይበግሩት ለብዙ ዓመታት ብዙዎች ሲመኙት የነበረውን መቀራረብንና መግባባትን ለማምጣት ቆርጦ ስራውን እያከናወነ ለዚህ ደረጃ መብቃቱንም ተናግረዋል፡፡
በዚህም ኮሚሽኑ እስካሁን በአስር ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ከ1ሺ በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን በማስመረጥ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ መሰብሰብ ስራውን እንደጀመረ አክለዋል፡፡
በቀጣይ ልክ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁሉ የተሳታፊዎች መረጣ በተካሄደባቸው ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስዳደር አጀንዳ እንደሚሰበስብ የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ በአማራና በትግራይ ክልሎች ደግሞ የተሳታፊዎች ልየታና መረጣ እንደሚያካሂድ ተናግረዋል፡፡
የአሁኑ ወጣት ትውልድ ከቀደሙት ትውልዶች ብዙ ተምሮ የተሻለ የሰላምና የእድገት ውርስ ይተዋል የሚል እምነት ኮሚሽኑ እንዳለውም አክለዋል፡፡
ከስብራት ህይወት ወጥተን ወደ ተሻለ ህይወት እንሸጋገር ዘንድ ወጣቱ ችግሩን በአጀንዳ ቀረፃ ጠብመንጃውን ወደ ሃሳብ መንጃና ማንሸራሸሪያ እንዲቀይር ኮሚሽኑ በትህትና ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የሀገራችን ችግር ወደ ሀገራዊ መፍትሄ ለማምጣት ኮሚሽኑ በምክክር ሂደት የሰላም በር በየትኛውም ቦታ ላሉ ወገኖች እንዲመቻች ጠንክሮ እንደሚሰራም ዋና ኮሚሽሩ አረጋግጠዋል፡፡
በተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አጀንዳውን በግልም ሆነ በጋራ ወደ ኮሚሽኑ ማምጣት እንደሚችል የጠቆሙት ዋና ኮሚሽሩ ምክክሩ አካታች እንደሚሆንና ሂደቱም ግልፅና ተዓማኒ በሆነ መልኩ እንደሚከወን በንግግራቸው አረጋግጠዋል፡፡
የአገራቸው ሰላም እና እድገት አሳስቧቸው የምክክሩ ሂደት እንዲሳካ ኮሚሽኑን እያገዙ ላሉ ሁሉ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡