የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

መንግሥት በሀገራዊ ምክክሩ መግባባት ላይ የሚደረስባቸውን ድምዳሜዎች ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ 4
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገር አቀፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን በአዲስ አበባ አስጀምሯል።
በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ በተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደ አንድ የምክክሩ ሂደት ባለድርሻ አካል መንግሥታቸውን ወክለው ተገኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በጦርነት እያለፈች እና በርካታ ስብራቶች እየገጠሟት ያለች ሀገር መሆኗን ገልፀዋል።
ከዚህ የጦርነት እና የስብራት ታሪክ ለመውጣት ምክክር ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አስምረውበታል።
“ዛሬ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ አዲስ ምዕራፍ ሁላችንም በንቃት ልንሳተፍ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ከተቃርኖ ይልቅ ተዛምዶን በማጠናከር፣ መጓደልን በመሙላት ኢትዮጵያን ተስፋ ያላት ሀገር ማድረግ የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ እንደሆነ ጠቁመዋል።
አክለውም በታሪክ ሂደት ተደጋግሞ የማይገኘውን ይህንን ታሪካዊ የምክክር አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም ሁላችንንም አሸናፊ ያደርገናል ሲሉም ተናግረዋል።በመሆኑም የትኛው አካል ይህ የምክክር እድል እንዳያመልጠው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስት በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ስራ ላይ በምንም ሁኔታ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሚሽኑን የሚመሩት ኮሚሽነሮችም በካበተ እውቀታቸውና ተሞክሯቸው ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ስራ ከመስራት ውጪ ሌላ ፍላጎት የላቸውም ሲሉም በኮሚሽነሮቹ ላይ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
በምክክሩ መግባባት ላይ የተደረሰባቸውን ድምዳሜዎች ለማስፈፀም መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማንስማማባቸው አጀንዳዎች የሚገጥሙን ከሆነም በህዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) እልባት ያገኛሉ ብለዋል። ሕዝብ ከወሰነ በኋላ ማናችንም ብንሆን የሕዝቡን ውሳኔ ማክበር ይኖርብናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በሀይል አማራጭ የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ጊዜያዊ አሸናፊና ተሸናፊ ፈጥሮ ከማለፍ በዘለለ ለችግራችን ዘላቂ መፍትሄ አያስገኝም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እያካሄደቸው ባለው ምክክር የሚከስር እንደሌለ ገልፀው በሂደቱ ሀገር አሸናፊ ትሆናለች ብለዋል።አዲስ 4