የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 348 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ሲያካሂድ የነበረውን የተሳታፊዎች ልየታ ስራ ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

mergedimages

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በአዳማ፣ በሀረር፣ በጅማ እና በሻሸመኔ ክላሰተር ሲያካሂድ የነበረውን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት ማጠናቀቁን በማስመልከት የመዝጊያ መርሀ-ግብር በሻሸመኔ ከተማ አካሂዷል፡፡

በዚህ የመዝጊያ መርሀ-ግብር የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን ዓርዓያ፣ ም/ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ እና ኮሚሽነር ተገኘወርቅ ጌጡ ( ዶ/ር) ተገኝተዋል::

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን ዓርዓያ ባደረጉት ንግግር በኦሮሚያ ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት በአራቱ ክላስተሮች 348 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮችን ያሳተፈ ስራ መጠናቀቁን አሳውቀዋል፡፡

ለዚህ ወሳኝ ሂደት መሳካት አስተዎፅኦ ላበረከቱ ሁሉ በኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በቀጣይ የልየታ ስራ ባልተጀመረባቸው ቦታዎች በተለይ በአማራና በትግራይ ክልሎች ኮሚሽኑ ስራዎችን ያከናውናል ብለዋል::

የኮሚሽኑ ም/ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ለብዙ ዘመናት ሳያግባቡን የነበሩ ጉዳዮችን ለመፍታት የተለያዩ ማህበረሰብን ወክላችሁ በአጀንዳ ልየታ ሂደት ላይ ለመሳተፍ በዚህ ወሳኝ ጊዜ በመመረጣችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል ብለዋል፡፡

ተወካዮች በቀጣይ የአካባቢያችሁ ማህበረሰብ የሚያነሷቸውን ሀገራዊ አጀንዳዎች በማሰባሰብ ብሎም በዋናው ሀገራዊ ምክክር ላይም በንቃት ለመሳተፍ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ከወዲሁ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል::