ኮሚሽኑ ዛሬ ከጅማ ክላስተር ከአሥር ወረዳዎች ተመርጠው ከመጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፤ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት አስጀምሯል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ተሳታፊዎች፣ ተባባሪ አካላት፣ የጅማ ማኅበረሰብ አባላትና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሂደቱን ለማገዝ ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በቅድመ ዝግጅት፣ በዝግጅትና በትግበራ ምዕራፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑንም ኮሚሽነር መላኩ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ተሳታፊዎች የተወከሉበትን የማኅበረሰብ ክፍል አውድ በተመለከተ በቂ ግንዛቤ ያዳበሩ እንዲኾኑ ለማድረግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዐት መዘርጋቱን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ገለልተኛ ተቋማትና አጋሮችን በማሳተፍ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑንና ወደፊትም እንደሚከናውን አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ተሳታፊዎች የሀገራዊ ምክክር ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም የአመራረጥ ሂደቱን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ማብራሪያ እየተደረገላቸው ነው፡፡
ዛሬ የተጀመረው የተሳታፊ ወኪሎችን የማስመረጥ ሂደት ለቀጣይ 10 ቀናት በጅማ ክላስተር ሥር ከሚገኙ 114 ወረዳዎች በሚመጡ ተሳታፊዎች በተመሳሳይ የሚቀጥል ይሆናል፡፡