የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሐረሪ ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን ከየማህበረሰብ ክፍሉ እንዲለዩ አድርጓል፡፡ በሐረር ከተማ ከሰኔ 5 እስከ ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው የተሳታፊዎች ልየታ መርሃ ግብር በክልሉ ከሚገኙ 9 ወረዳዎች የተውጣጡ 9 የማህበረሰብ ክፍሎች እያንዳንዳቸው 50 ሰዎችን መርጠው በሂደቱም ከ 4,000 በላይ ተሳታፊዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡ በዚህም መሰረት በክልሉ በተደረገው የተሳታፊዎች ልየታ 324 ተወካዮች በቀጣይ ለሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ እንዲወከሉ በክልሉ ከሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተመርጠዋል፡፡
በሌላ በኩልም ተሳታፊዎች በቡድን ባደረጓቸው ውይይቶች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲነሱ የሚፈልጓቸውን አጀንዳዎች ያመላከቱ ሲሆን በተወካዮቻቸውም አማካኝነት በክልል በሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ያመላከቱዋቸው አጀንዳዎች እንደሚንፀባረቁላቸው ይጠበቃል፡፡