የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ኮሚሽኑ በአፋር ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚወከሉትን ተወካዮች እንዲመረጡ የማድረግ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮችን ከህዳር 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከየማህበረሰብ ክፍሉ እንዲመረጡ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ሂደቱም በተለያዩ ምዕራፎች የሚከናወን ሲሆን ዛሬ በተጀመረው የመጀመሪያው ዙር መርሀ-ግብር ላይ ከዞን አንድ ሰመራ እና ሎጊያ ወረዳዎች በሂደቱ ላይ ተሳታፊዎች በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡

የክልሉ ርዕሰ-መዲና በሆነችው ሰመራ ከተማ ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ መርሀ-ግብር ከሰመራና ሎጊያ ወረዳዎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች ወኪሎቻቸውን እንዲመርጡ በማድረግ የሚጀምር ሲሆን በመቀጠልም በዞን አንድ ውስጥ ካሉ ሌሎች አስር ወረዳዎች ተወካዮችን የማስመረጡ ሂደት ይቀጥላል፡፡

በክልሉ በአጠቃላይ ከ50 በላይ ከሚሆኑ ወረዳዎች የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የሚካሄደው ይህ ሂደት በድምሩ ከ3,800 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮችን ያሳትፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሂደቱም ከእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል አስር አስር ሰዎች የሂደቱ ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡

በዛሬው ዕለት እየተካሄደ በሚገኘው የተወካዮች መረጣ በአጠቃላይ 160 ተሳታፊዎች ተካፋይ በመሆን ላይ የሚገኙ ሲሆን 36 ተወካዮች እና 9 ተጠባባቂዎች ተመራጭ እንደሚሆኑበት ይጠበቃል፡፡ በመርሀ-ግብሩ መሰረት ለተሳታፊዎች ስለምክክር ፅንሰ ሀሳብ፣ ኮሚሽኑ ስላከናወናቸው ተግባራት፣ ሰለሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ለተሳታፊዎች ገለፃ በመደረግ ላይ ነው፡፡ በመቀጠልም ተሳታፊዎች ለአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ይወክሉናል የሚሏቸውን ሁለት ሁለት ግለሰቦች ከአንድ ተጠባባቂ ጋር በየወረዳቸው እና በየማህበረሰብ ክፍሎቻቸው ይመርጣሉ፡፡

በቀጣዮቹ ቀናትም ኮሚሽኑ የሚያስተባብረው የተወካዮች መረጣ በተመሳሳይ ሁኔታ በዱብቲ፣ አሳይታ፣ ጭፍራ፣ አዳአር፣ ሚሌ፣ ኢሊዳር እና ኮሪ ከተሞች ይቀጥላል፡፡