ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ አካላት ጋር ተወያይቶ አጀንዳቸውን ተቀበለ
ጥር 28/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ እና የሰላምን መንገድ መርጠው ከተመለሱ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡
የመድረኩን ዓላማ በማስተዋወቅ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ቡድኑ ሰላምን በመሻት እና ኮሚሽኑ ሲያቀርባቸው የነበሩ የምክክር ጥሪዎችን በመቀበል ወደ ምክክር እና ሰላም መንገድ በመምጣታቸው አመስግነው ይህም ለሀገራችን ሰላም ትልቅ እምርታ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ኮሚሽኑን በመወከል የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) የኮሚሽኑን አመሰራረት፣ ያከነወናቸውን ዐበይት ተግባራት፣ ስኬቶቹን እና ፈተናዎቹን እንዲሁም በቀሪዎቹ ጊዜያት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አብራርተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዋና ኮሚሽነሩ በአማራ ክልል የተከናወነውን የምክክር ሂደት በተመለከተም ገለፃ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ነፍጥ አሸናፊ እና ተሸናፊን የሚፈጥር እንጂ ሀገራዊ መግባባትን የሚያሰፍን እንዳልሆነ የገለፁት ዋና ኮሚሽነሩ ሀገራዊ መግባባት የሚሰፍነው ሁሉም አካላት ስለሀገራቸው ለመመካከር ባላቸው ፅኑ ፍላጎት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ ነፍጥ አንስተው ወደ ጫካ ያስገቧቸውን ጉዳዮች ጨምሮ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ የሚኖራቸውን አጀንዳዎችን አደራጅተው በዚሁ መድረክ በውይይት አዳብረው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
የርክክብ መድረኩን በንግግር የዘጉት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ ቡድኑ ያለውን ጥያቄ በሰለማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረገውን ጥረት አድንቀው ቡድኑ የምክክር ሂደቱ አካል በመሆኑ ያላቸውን አክብሮት ገልፀዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ኮሚሽኑ የተረከበውን አጀንዳ ለኮሚሽኑ ምክር ቤት በማስረከብ እና የአጀንዳ ቀረፃ በማድረግ አጀንዳዎቹን ለሀገራዊ ምክክር ግብዓት እንደሚያቀርባቸው ገልፀዋል፡፡
ኮሚሽኑ በተለያዩ መንገዶች አጀንዳ ማሰባሰቡን ይቀጥላል፡፡





