የጃፓን መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን 12 ተሸከርካሪዎችን በዛሬው ዕለት አስረክቧል፡፡
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ልገሳው የጃፓን መንግሥት ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ያለውን ድጋፍ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለሚያከናውናቸው ተግባራት ቅልጥፍና ልገሳው ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ለምትሰራው ስራ የጃፓን መንግሥት ወደፊትም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አምባሳደሩ ያረጋገጡት፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ተወካይ ሳሙኤል ዶው በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት በእጅጉ አስፈላጊ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ለኮሚሽኑ በርካታ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ ወደፊትም በአጋርነት እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ በርክክቡ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ኮሚሽኑ በምክክር ሀገራዊ መግባባት እንዲሰፍን ለማድረግ እየሠራ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም አጋር አካላት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት እያደረጉት ያለው ድጋፍ የማይተካ በመኾኑ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ድጋፎቹ የኮሚሽኑን ዓላማ ለማሳካት እንደሚጠቅሙ ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትና መግባባት እንዲፈጠር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በርክክብ ሥነ ሥርዐቱ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ ሠራተኞች፣ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ኃላፊዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር እና ሰራተኞች ተገኝተዋል፡፡