የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

እስረኞች እንዲፈቱና በክልሉ ያለው ግጭት እንዲቆም ኮሚሽኑ ጠየቀ

fb img 1741948778095

እስረኞች እንዲፈቱና በክልሉ ያለው ግጭት እንዲቆም ኮሚሽኑ ጠየቀ

መጋቢት 5/2017 ዓ.ም

በዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) የተመራ የኮሚሽኑ ልዑክ ትላንት መጋቢት 4/2017 ዓ.ም ወደ አማራ ክልል ባህርዳር ከተማ አቅንቶ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

የኮሚሽኑ ልዑክ ወደ አማራ ክልል ያቀናው የአማራ ክልል የአጃንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ በሚካሄድበት አስቻይ ሁኔታ ላይ ከክልሉ መንግስት ጋር ለመነጋገር ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በተገኙበት በዚህ ውይይት የኮሚሽኑ የእስካሁን ስራዎች በዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ(ፕሮፌሰር) ቀርቦ የክልሉ አመራሮች ስለ ኮሚሽኑ የስራ እንቅስቃሴ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል።

ከኮሚሽኑ የቅርብ ጊዜ የስራ እቅዶች መካከል አንዱ በአማራ ክልል የአጀንዳ ልየታ የምክክር ምዕራፍ ማካሄድ ስለመሆኑ የኮሚሽኑ ልዑኩ ለክልሉ አመራሮች አሳውቋል።

በክልሉ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይላት ወደ ሰላም ንግግር እንዲመጡ የክልሉ መንግስት እያደረገ ያለውን የሰላም ጥሪ ጥረት ያደነቀው የኮሚሽኑ ልዑካን ቡድን ሆኖም አሁንም መሰራት አለባቸው ያላቸውን ስራዎች ጠቁሟል፡፡

ኮሚሽኑ ምክክሩን አካታች በሆነ ሁኔታ ማከናወን እንዲችል በማንኛውም አካባቢ የታሰሩ እስረኞች እንዲፈቱ የክልሉ መንግስት በራሱ በኩል እርምጃ እንዲወስድ እንዲሁም በሌሎች ላይም ግፊት እንዲያደርግ ልዑኩ ጠይቋል፡፡

በክልሉ ያለው ግጭት ቆሞ አስቻይ የምክክር ሁኔታ እንዲኖር መንግስት ተኩስ አቁሜአለሁ ብሎ በማወጅ የመጀመሪያውን እርምጃ እንዲወስድም ነው የኮሚሽኑ ልዑክ አፅንኦት ሰጥቶ የጠየቀው፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት እስካሁን ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ በክልሉ የሚያካሂደው የምክክር መድረክ እንዲሳካም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ምክክሩ አሳታፊና አካታች በሆነ አስቻይ ሁኔታ እንዲካሄድም ኮሚሽኑ ያቀረባቸው ጥያቄዎች በክልሉ መንግስት በኩል ተገቢው ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡