ታህሳስ 13/2017 ዓ.ም
የዜጎችን ሰላም ለማስፈን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ምክክር አስፈላጊ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እየተሳተፉ የሚገኙ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሰራዊት አባላት ተናገሩ፡፡
በቅርቡ ከመንግስት ጋር የሰላም ስምምነት የተፈራረመው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሰራዊት ከፍተኛ አመራር ጃል ሰኚ ነጋሳ የምክክሩን አስፈላጊነት አፅኦት ሰጥቶ፣ የኦሮሞ ህዝብም ምክክሩ ሰላም ያመጣል የሚል እምነት እንዳለው ገልጧል፡፡
ምክክሩ ምሉዕ የሚሆነው ሁሉም ዜጋ ሲሳተፍበት መሆኑን የተናገረው አመራሩ ለዚህም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሁሉ እንደነሱ የሰላም ስምምነት ፈፅመው በዚህ የምክክር መድረክ እንዲሳተፉ ነው ጥሪ ያቀረበው፡፡
በምክክር መድረኩ ሃሳቦችን በነፃ አንስተን፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተከራክረን፣ ለዜጎች ሰላምና ደህንነት የሚጠቅሙ ሀሳቦችን ይዘን ስንወጣ ነው ምክክሩ የተሳካ የሚሆነው ያለው ጃል ሰኚ ነጋሳ ለዚህም ሁላችንም ለምክክሩ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህንን የምክክር መድረክ በማመቻቸቱ ምስጋና አቅርቧል፡፡