የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የኦሮሚያ ክልል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በይፋ ተጀመረ

111111 min
ታህሳስ 13/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስተባባሪነት ከታህሳስ 7/2017 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ሁለተኛው ምዕራፍ የሆነው የባለድርሻ አካላት ምክክር ዛሬ ታህሳስ 13/2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ጨፌ ኦሮሚያ መሰብሰቢያ አዳራሽ በይፋ ተጀምሯል፡፡
በዚህ መድረክ 320 የህብረተሰብ ወኪሎችን ጨምሮ ከ1ሺ 700 በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አካላት፣ የተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም የማህበራትና ተቋማት ወኪሎች መሳተፍ ጀምረዋል፡፡
ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አንድ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት በሚገኙት በዚህ ምክክር ቀደም ሲል በክልሉ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ነገር ግን በቅርቡ ከመንግስት ጋር የሰላም ስምምነት ፈፅመው የተመለሱ ታጣቂዎችም እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ይህንን መድረክ በንግግር የከፈቱት የኦሮሚያ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ አስተባባሪ ኮሚሽነር አምባዮ ኦጋቶ (ዶ/ር) በምክክር ሂደቱ የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
በሀገራችን ለዘመናት የዘለቀ መሠረታዊ ችግር ለመፍታት በመደማመጥ መንፈስ መነጋገር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። አክለውም ከተደማመጥን ጠንካራ ማህበረሰብና ሀገር መፍጠር እንችላለን ሲሊ አስረድተዋል።
በኦሮሚያ ክልል የምክክር ሂደት ድጋፍና አመራር እየሰጡ የሚገኙት ሌላኛው ኮሚሽር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ምክክር እውነትን ፍለጋ መሆኑን አንስተው ፍቅር፣ ሰላምና አንድነትን ለማስፈን መመካከር አስፈላጊ መሆኑን አፅኦት ሰጥተዋል፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽር ሂሩት ገ/ስላሴ ኢትዮጵያን በሃላፊነት ስሜትና በጥበብ መምራት አለብን ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የምክክሩ ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ በማንሳት ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎች እንዲለዩ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አሳስበዋል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በበኩላቸው የኦሮሞ ህዝብን የመመካከር ባህል ተጠቅመው ለምክክሩ መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለምክክሩ ባለድርሻ አካላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) በኢትዮጵያ በሀሳብ መሪዎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች የሚስተዋሉ ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ኮሚሽኑ በአዋጅ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ በአብዛኞቹ ክልሎች መሰል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮችን በዘጠኝ ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ማጠናቀቁንም ገልፀዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልልም የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር በቀጣይ ሶስት ቀናት ተከናውኖ እንደሚጠናቀቅም ዋና ኮሚሽሩ አስታውቀዋል፡፡
ዛሬ የተጀመረው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እስከ መጪው ማክሰኞ ታህሳስ 15/2017 ዓ.ም ድረስ በቡድን በሚደረጉ ምክክሮች የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ባለድርሻ አካላቱ በመጪው ማክሰኞ ታህሳስ 15/2017 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልል አጀንዳዎችን ለይተው ለኢትጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያስረክባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡