የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎቹን ለኮሚሽኑ አስረከበ።
ጥር 29/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሊካተቱ ይገባሉ ያላቸውን አጀንዳዎች በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በይፋ አስረክቧል፡፡
በርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ ኮሚሽኑን ወክለው ንግግር ያደረጉት ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ፤ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ ለኮሚሽኑ ዓላማ መሳካት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ስለ ኮሚሽኑ ተግባራት መረጃ እንዲያገኝ በማድረግ እንዲሁም የሚዲያ ተቋማትን ሀገራዊ አጀንዳዎች አደራጅቶ በማስረከቡ ለምክር ቤቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይ የምክክር ሂደትም ምክር ቤቱ ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፤ ምክር ቤቱ በሥነምግባር የታነጸ ሚዲያ በሀገራችን እንዲጎለብት የሚሠራ ተቋም ነው ብለዋል፡፡
አክለውም ምክር ቤቱ በስድስት ርዕሰ ጉዳዮች የተከፋፈሉ የሀገራችንን እንዲሁም የሚዲያ ኢንዱስትሪውን መሠረታዊ ችግሮች የሚፈቱ አጀንዳዎች መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ከሀገራዊ ምክክሩ ጋር የሚተሳሰሩ ጉዳዮችን ወደ ሕዝብ ለማስረጽ በትኩረት መሥራቱን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በአጀንዳ ርክክብ ሥነሥርዐቱ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች፣ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ አባላትና ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡