የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀጣይ አንድ ዓመት አበይት ተግባራት
የካቲት 27/2016 ዓ.ም
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሶስት ዓመታት የስራ አፈፃፀም በማዳመጥ እና ያልተከናወኑ ተግባራትን ከግምት ውስጥ በማስገባት የኮሚሽኑን የስራ ዘመን ለአንድ ዓመት ማራዘሙ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ መሰረት ኮሚሽኑ ሀላፊነቱን እንዲወጣ በተጨማሪነት በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚከተሉትን ተግባራት ያከናውናል፡፡
- በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን ማከናወን እንዲሁም በትግራይ ክልል የተባባሪ አካላት ስልጠና፣ የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፎችን ማካሄድ፤
- በፌደራል ደረጃ ከሚገኙ ተቋማት እና ማህበራት ተወካዮች የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክን ማዘጋጀት፤
- ከዲያስፖራው ተሳታፊዎችን መለየት እና አጀንዳን መሰብሰብ፤
- በተለያየ መልኩ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን ማጠናከር፣ መለየት፣ በየጭብጡ ማዘጋጀት፣ ቅደም ተከተል ማስያዝ፣ ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ማቅረብ፣ ተለይተው በተደራጁ አጀንዳዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት፣ አጀንዳዎችን በኮሚሽኑ ምክር ቤት በመቅረጽ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፤
- የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አወያዮች እና አመቻቾችን መለየት፣ ማሰልጠን እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ፤
- ሀገር አቀፍ ንቅናቄን በማካሄድ የግንዛቤ ስራዎችን በማስፋት የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር ማስቻል ብሎም የሕዝብ ባለቤትነትን ማረጋገጥ፤
- አሳታፊና አካታች የሆነ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤን ማካሄድ፤
- ከምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሀሳቦችን ማጠናቀር፣ ምክረ ሀሳብ ማዘጋጀትና ተፈፃሚነታቸውን መከታተል፤
- የዶክመንቴሽን ስራዎችን ዲጂታላይዝድ ማከናወን እና ተደራሽነቱን ማስፋት ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት እንደ አስፈላጊነቱ እና ድጋፍን በተጠየቀ ወቅት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ከፍተኛ ነበር፡፡
በመጪውም አንድ ዓመት ለሚያከናውናቸውም ተግባራትም የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይታመናል፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!