- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሰኞ መጋቢት 16/2016 ዓ.ም ጀምሮ በጅማ ክላስተር የ114 የወረዳና የከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች በአጀንዳ ማሰባሳቢያ ህዝባዊ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን የሚመርጡባቸው መድረኮችን እያካሄደ ነው፡፡
እስከ ዛሬ አርብ ድረስ 57 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ተወካዮቻቸውን መምረጥ ችለዋል፡፡ በሂደቱ ከ4ሺ 500 በላይ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
የጅማ ክላስተር የጅማ ዞንን ጨምሮ፣ ከቡኖ በደሌ፣ ኢሉ አባቦር፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች የመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአጀንዳ ማሰባሳቢያ ህዝባዊ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን የሚመርጡበት ክላስተር ነው፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ ባለው ሂደት ከጅማ፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉ አባቦርና ምሥራቅ ወለጋ የመጡ የ56 ወረዳዎች ተሳታፊዎች ተወካዮቻቸውን መርጠዋል፡፡
ከምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች የመጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በቀጣይ ቀናት በአጀንዳ ማሰባሳቢያ ህዝባዊ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ፡፡
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች በአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመለየት ስራ ከማክሰኞ መጋቢት 17/2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ነው፡፡
በእነዚህ ዞኖች በአጠቃላይ በ36 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች በቀጣይ በአጀንዳ ማሰባሰቢያ ህዝባዊ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን እየመረጡ ነው፡፡
እስከ ዛሬ አርብ ድረስ 32 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ተወካዮቻውን መርጠዋል፡፡
ተወካዮችን በምረጥ ሂደቱ 3ሺ 200 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
እስካሁን ያለው ሂደት አካታችና አሳታፊ እንዲሁም በኢትዮጵያ በሂደት ላይ ስላላው ሀገራዊ ምክክር ግንዛቤ ያገኙበት እንደነበር ተሳታፊዎቹ የገለጹባቸው መድረኮች ተካሂደዋል፡፡
- ኮሚሽኑ ከመጋቢት 16 እስከ 17/2016 ዓ.ም በአጀንዳ ማሰባሰቡ ሂደት ላይ እገዛ የሚያደርጉ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የመጡ108 አወያይ መምህራንን በዚሁ ሳምንት አሰልጥኗል፡፡
ስልጠናውን የወሰዱ መምህራን ኮሚሽኑ ለሚያካሂደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት በሞደሬተርነት እና ከኮሚሽኑ ጎን በመሆን የበኩላቸውን አስተዎጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው፡፡
ኮሚሽኑ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚያከናውነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ግልፅኝነት፣ አሳታፊነት እና ተዓማኒነት እንዲኖረው ስልጠናውን የወሰዱ መምህራን ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸውም ተብሏል፡፡
- ከተለያዩ ምንጮች የአጀንዳ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ የሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች በዚህም ሳምንት ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለው አሰራር መሰረት የአጀንዳ ሀሳቦችን ከተቋማት፣ ማህበራትና ግለሰቦች ማሰባሰቡን ቀጥሏል፡፡ በተለይ የኮሚሽኑን ድረ ገጽ በመጠቀም በርከት ያሉ የአጀንዳ ሀሳቦች እየደረሱት ነው፡፡ ሀገር ሊመክርበት ይገባል ብለው ያሰቧቸውን አጀንዳዎች የላኩልንን በጣም እናመሰግናለን፡፡
አሁንም የአጅንዳ ሀሳብ አለን የምትሉ ወገኖች በድረገጻችን https://ethiondc.org.et/ እንድትልኩ ተጋብዛችኋል፡፡