የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል ውይይት አድርጓል፡፡ በኮሚሽኑ አዘጋጅነት የተደረገው የዚህ ውይይት ዓላማ ኮሚሽኑ በጋራ ምክር ቤቱ አጋዥነት በሰራቸው ስራዎች ላይ ገለፃ ለመስጠት እና በቀጣይም በሚሰራቸው ስራዎች ላይ ውይይቶችን ለማድረግ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን ከየማህበረሰብ ክፍሉ ሲያስመርጥ የሂደቱን ግለፀኝነትና እና ተዓማኒነት በማረጋገጥ ረገድ ለኮሚሽኑ እገዛን ሲያደርጉ ከነበሩ ተባባሪ አካላት መካከል የኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አንዱ እነደሆነ የሚታወስ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ኮሚሽኑ ተሳታፊዎችን ለመለየት በተንቀሳቀሰባቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የፖሊቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ለኮሚሽኑ ትልቅ እገዛን እንዳደረገ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በውይይቱ ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች እና ገንቢ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን ኮሚሽኑ በተሳታፊዎች ልየታ ሂደት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሊያስተካክላቸው ስለሚገባቸው ነገሮች ሀሳቦችና እና አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በውይይቱ ላይ እንደጠቀሱት ሁሉም በትጥቅ ትግል ወይም በሰላማዊ መንገድ ተሰልፈው ያሉ የፖለቲካ ሀይሎች የሀገራዊ ምክክሩ አካል እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ባቀረባቸው መሰል ጥሪዎች ምላሽ በመስጠት በዝግጅቱ ላይ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ተወካዮች ፓርቲውን ወክለው የተገኙ ሲሆን ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ ለመስራት ያላቸውን ፈቃደኝነትም ገልጸዋል፡፡