የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ልየታ ምክክር ምዕራፍ ተጠናቀቀ፡፡

አዲስ 2
ለሰባት ተከታታይ ቀናት በአደዋ ሙዚየም መታሰቢያ አዳራሽ ሲከናወን የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ መቋጫውን አግኝቷል፡፡
በምክክር መድረኩ ሰባተኛ ቀን ውሎ ከኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች፣ ከሦስቱ የመንግሥት አካላት ተወካዮች፣ ከማኅበራት እና ተቋማት ተወካዮች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተወካዮች የተመረጡ ወኪሎች የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን አደራጅተው ለጠቅላላ መድረኩ አቅርበዋል፡፡
ተሳታፊዎች የቀረቡትን አጀንዳዎች መነሻ አድርገው የተለያዩ ሀሳቦችን ካንሸራሸሩ በኋላ የከተማዋን አጀንዳዎች ለይተው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
የምክር ምዕራፉን መጠናቀቅ አስመልክተው ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) “በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ልዩነቶችን በውይይት ማስተናገድ እንደሚቻል ያሳየ ነው” ብለዋል፡፡
በሂደቱ የሀሳብ ልዩነቶችን በአንድ መድረክ ማስተናገድ የሚቻልበት ልምምድ መፈጠሩን የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የተሳተፉ አካላት በቀጣይ ጊዜያትም ያልተነሱ የሚሏቸውን አጀንዳዎች በግልና በቡድን ለኮሚሽኑ ማቅረብ እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ በሌሎች ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንደሚከናወን ዋና ኮሚሽሩ በማብራሪያቸው ጠቁመዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ በአዲስ አበባ ደረጃ የተከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እዲሳካ አስተዋፅ ላደረጉ አካላት እና ለተሣታፊዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡አዲስ 2