የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የአማራ ክልል የምክክር ምዕራፋ በይፋ ተጀመረ

img 20250405 112421 572

“ባለመመካከራችን ብዙ ዋጋ ከፍለናል፤ እንመካከር”- ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር)

መጋቢት 27/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) ይህንን መልዕክት ያስተላለፉት ዛሬ መጋቢት 27/2017 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ የተጀመረውን የምክክር መድረክ በንግግር ሲከፍቱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስተባባሪነት በአማራ ክልል የሚከናውነው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ ፔዳ ካፓስ ስታድየም በይፋ ተጀምሯል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) በኢትዮጵያ ያሉ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት መመካከር ወሳኝና ብቸኛው መፍትሄ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ እጅግ መሠረታዊ የአለመግባባት መንስኤዎችን ከስር መሰረታቸው በመለየት በአጀንዳ መልክ በማሰባሰብ ስኬታማ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለመመካከራችንና ችግሮቻችንና በሀይል አማራጭ ለመፍታት በመሞከራችን ዋጋ አስከፍሎናል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ ሁሉም ወገኖች ወደዚ ሁሉንም አሸናፊ ወደሚያደርገው ምክክር እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የምክክር አጀንዳዎች በመለየት ለኮሚሽኑ እንዲያስረክቡም አሳስበዋል፡፡

የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ በሂደቱ ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት ሁሉ ዋና ኮሚሽሩ በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል።

በአማራ ክልል የምክክር መድረክ ከክልሉ ወረዳዎች አስር የማህበረሰብ ክፍሎችን ወክለው የተመረጡ ከ4ሺህ 500 በላይ የህብረተሰብ ወኪሎች ከዛሬ መጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምረው ለተከታታይ አምስት ቀናት የአጀንዳ ሃሳቦቻቸውን በውይይት የሚያጠናቅሩ ይሆናል፡፡

በዚህ የምክክር ሂደት ሁለተኛ ምዕራፍ የተመረጡ የወረዳ ማህበረሰብ ክፍል ወኪሎችን ጨምሮ የመንግሰት ፣ የተቋማትና ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወኪሎች አጀንዳዎቻቸውን በውይይት አዳብረው በማጠናቀር ሚያዚያ 4/2017 ዓ.ም ለኮሚሽኑ እንደሚያስረክቡ ይጠበቃል፡፡

በአማራ ክልል የምክክር መድረክ ከአምስቱ የምክክር ባለድርሻ አካላት በጥቅሉ ከ6ሺህ በላይ ወኪሎች እንደሚሳተፉም የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡