የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተጀመረ

img 20250410 111730 282

በእስር ላይ የሚገኙ፣ ለትግል ጫካ የገቡ እንዲሁም በስደት ላይ ያሉ ወገኖች አጀንዳ የሚሰጡበት ሁኔታ ይመቻቻል- ኮሚሽኑ

ሚያዚያ 2/2017 ዓ.ም

በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ፣ለትግል ጫካ የገቡ እንዲሁም ከሀገር የተሰደዱ የአማራ ክልል ተወላጆች ስለ አማራ ክልል እንዲሁም ሰለ ሀገራቸው ሀሳብ የሚሰጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስተውቋል።

የአማራ ክልል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክን በንግግር የከፈቱት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ኮሚሽኑ ይህንን ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ሰፋፊ በሆኑ ህዝባዊ ምክክሮች አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ አጀንዳዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱን ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል፡፡

በአማራ ክልልም ከመጋቢት 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና በሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

እንደ ኮሚሽነር መላኩ ገለፃ ኮሚሽኑ በሀገር ውስጥም በውጪም ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ የዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል አድርጎ ተግባሩን ማከናወኑን ይቀጥላል።

ስለሆነም በእስር ቤት ያሉ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ጫካ የገቡ እንዲሁም ሀገራቸውን ለቀው በውጪ ሀገራት የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ሁሉ ሃሳባቸውን የሚሰጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ኮሚሽኑ ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አረጋግጠዋል።

በአጠቃላይ አማራ ክልልን ጨምሮ እንደ ሀገር በትጥቅ ትግል፣ በእስርና በስደት የሚገኙ ዜጎች ብቸኛ እና በጣም አዋጭ በሆነው የምክክር ሂደት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በምንም ምክንያት ቢሆን አንድም ወገን ከምክክር ሂደቱ እንዳይቀር የተከበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግፊት እንዲያደርግና እስከዛሬ ለኮሚሽኑ ሲያደርግ የቆየውን ብርቱ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል በኮሚሽኑ ስም ጥሪ አስተላልፈዋል።

ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) በበኩላቸው ምክክር እውነትን የማፈላለግ ሂደት ነው ሲሉ ገልፀውታል።

እውነት በጠብ፣ በግጭት፣ በጠመንጃ ተፈልጋ አትገኝም ያሉት ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) እውነት በምክክር ብቻ ነው የምትገኘው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለማረጋገጥ፣ ህግና ሥርዓት የበለጠ እንዲጎለብት እንዲሁም ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ምክክር የማዕዘን ድንጋይ ነው ሲሉም አክለዋል።

በመሆኑም በአማራ ክልል ምክክር ላይ የተገኙ ባለድርሻ አካላት ለአማራ ህዝብና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሰላም ይበጃል ያሉትን ሀሳብ በማፍለቅ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዛሬ የተጀመረው የአማራ ክልል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ እስከ መጪው ቅዳሜ የሚቀጥል ይሆናል።

በሂደቱ ከ2ሺ በላይ የአምስቱ ባለድርሻ አካላት ወኪሎች መሳተፍ ጀምረዋል።