የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የባለድርሻ አካላት አስተዋፅኦ

00
የባለድርሻ አካላት አስተዋፅኦ
ግንቦት 7/2017 ዓ.ም
ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት መሳካት በሁለት መልኩ የሚገለጹ ኃላፊነቶችን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው በተለያዩ ሀገራት የተከናወኑ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ያሳያሉ፡፡
እነዚህም ለምክክር ሂደት ምቹ ሁኔታን መፍጠር እና እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በምክክር ሂደት ላይ መሳተፍ ናቸው፡፡ በዝርዝር ለማየት የሚከተሉት ቀርበዋል፡፡
👉መተማመንን መፍጠር
ማኅበረሰቡ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ እምነት እንዲኖረውና የመንግሥት ጣልቃገብነት እንዳይፈጠር መሥራት፣ የሕዝብ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ማረጋገጥ፣ የመገናኛ ብዙኃንን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የፖለቲካ ውጥረቶች እንዲረግቡ ጥረት ማድረግ፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር በጋራ መሥራት፣ ግጭቶች እንዲቆሙ እና የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡
👉የሕግ የበላይነት እና መልካም አስተዳደርን ማስፈን
ባለድርሻ አካላት ከሆኑ ተቋማት መካከል መንግሥት ዋነኛው ነው፡፡ መንግሥት በምክክር ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማጠናከርና መልካም አስተዳደርን ከምንግዜውም በላይ ማስፈን ይጠበቅበታል፡፡ የሕግ የበላይነትና መልካም አስተደዳር እየጎለበተ ሲሄድ ማኅበረሰቡ በምክክር ሂደቱ ላይ አመኔታው ይጨምራል፡፡ ይህ መተማመን ደግሞ ለሀገራዊ መግባባት ምቹ መደላድል ይፈጥራል፡፡
👉የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን ማከናወን
ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ መግባባት ያላቸውን ሚና ለመወጣት ህዝቡን ማንቃት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሀገራዊ መግባባትን ምንነትና አስፈላጊነት በተመለከተ የተቀናጀ ስራ በመስራት ህዝቡን ወደ መግባባት የሚወስዱ ጎዳናዎችን አቋሞችን እንዲይዙ ግንዛቤን የመስጨበጥ ተግባር ማከናወን ይገባቸዋል፡፡
👉መደበኛና ኢመደበኛ የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀት
ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር መደበኛና ኢመደበኛ የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ እነዚህ መድረኮች የማይግባቡ ግለሰቦችን፣ ፓርቲዎችን፣ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በአነስተኛ ቁጥር በማቀራረብና በጥልቀት በማወያየት ለሀገራዊ መግባባት ሂደት የበኩላቸውን እገዛ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ እነዚህን መድረኮች ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ወይም በተናጥል ሊያዘጋጁ ይችላሉ፡፡
👉በጎ ተጽዕኖን መፍጠር
በሀገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና፣ ዝናና ተደማጭነት ያላቸው ግለሰቦች፣ ተቋማት እንዲሁም ማኅበራት ለሀገራዊ መግባባት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሚና እንደሚኖራቸው ይገመታል፡፡
ያላቸውን ተደራሽነትና ተቀባይነት በመጠቀም ሀገር እንድትግባባ በሚደረገው ጥረት የራሳቸውን አሻራ ሊያስቀምጡ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ መምህራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ደራሲዎች፣ ማህበራዊ አንቂዎች፣ ስፖርተኞች፣ መምሕራን፣ በዚህ ረገድ ድርሻቸው የላቀ ነው፡፡
እነዚህ አካላት አብሮነትን፣ የሀገር ፍቅርን፣ መተባበርን፣ መተማመንን፣ ሰላምን ወዘተ የሚያስተጋቡ ሀሳቦችን በተለያየ መልኩ ወደ ህዝቡ በማድረስ ለሀገራዊ መግባባት አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ፡፡
                                                ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!