የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የምክክር ሂደት ተሳታፊዎች

አካታችና አሳታፊ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሚመራባቸው መሠረታዊ መርሆዎች መካካል አንዱ አሳታፊነትና አካታችነት ነው፡፡ በመሠረቱ ሁለቱ ጽንሰ ሀሳቦችን ለያይቶ መመልከት የሚቻል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአፈጻጻም  ረገድ ተቆራኝተው የሚተገበሩ ናቸው፡፡ አሳታፊ ሆኖ የማያካትት ወይም አካታች ሆኖ በሚገባው ልክ የማያሳትፍ የምክክር ሂደት ውጤታማ የመሆን እድሉ እጅግ ጠባብ ነው፡፡

ይህንንም ግምት ውስጥ በማስገባት ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ በየደረጃው መሳታፍ ያለባቸው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት እንዲካተቱና በሚገባው ልክ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማደረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ሰፊው ህብረተሰብ ጎጥ፣ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ክፍለ ከተማ፣ ዞን፣ ልዩ ወረዳ፣ ክልል በሚባሉ መዋቅሮች ተሳስሮ እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ የሚካሄደው ምክክር አሳታፊና አካታች እንዲሆን ተሳታፊዎችን የመለየቱ ተግባር ምንን መሠረት አድርጎ መከናወን አለበት? ከየትስ መጀመር አለበት? አካሄሄዱስ ምን መሆን አለበት? ለሚሉ አንኳር ጥቄዎች ምላሽ ለማግኘት ጊዜ ወስዶ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ የነዚህ ሂደቶች ውጤት የሆነም የተሳታፊ ልየታ የአሰራር ስነ ዘዴን ማበልጸግ ተችሏል፡፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግ ዋና ዋና ጉዳዮች ቀጥሎ ቀርበዋል፡፡

የምክክር ተሰታፊዎች ልየታ የትኩረት ቦታዎች

focus areas

በነዚህ የትኩረት ቦታዎች ተሳታፊዎች የሚለዩበት ሁኔታና የተሳታፊዎች ስብጥር እንደየሁኔታው የተለያየ አካሄድን ሊከተል ይችላል፡፡

ከወረዳ ተሳታፊዎችን የመለየት ሂደት

ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው በኢትዮጵያ ከጎጥ እስከ ፌደራል የሚደርሱ መዋቅሮች አሉ፡፡ ምክክሩን አሳታፊና አካታች ለማድረግ በተለይም ሰፊውን ህብረተሰብ ለማካተት ከየት መጀመር አለበት የሚለው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ማግኘት ነበረበት፡፡ በኢትዮጵያ ክፍለ ከተሞችንና የከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ከ 1ሺ 300 የሚሆኑ ወረዳዎች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ወረዳ በአማካይ 10 ቀበሌዎች አሉት ቢባል ከ13ሺ የማያንሱ ቀበሌዎች ይኖራሉ እንደማለት ነው፡፡ አንድ ቀበሌ በአማካይ 7 ጎጦች ቢኖሩት ከ91ሺ በላይ ጎጦች ይኖራሉ እንደማለት ነው፡፡

ኮሚሽኑ ስራውን አከናውኖ ለማጠናቀቅ ካለው ውስን ጊዜና አቅም፣ ምክክሩ በሂደቱ ሊያሳትፋቸው የሚችሉ ሰዎችን ቁጥር ከመወሰን እንዲሁም ከሌሎች መመዘኛዎች አኳያ ከየት ይጀመር የሚለው ጉዳይ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ያሉ አማራጮችን ሁሉ ጠረጴዛ ላይ በማስቀመጥ የሚመለከታቸውን አካላት ጭምር በማሳተፍ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት ከወረዳ እንዲጀመር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በዚሁ መሰረት ወረዳዎች ያሏቸውን ቀበሌዎች ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ውክልና በሚያረጋግጥ አግባብ የምክክር ሂደት ተሳታፊዎች ልየታ በሁለት ደረጃ እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ተሳታፊ ልየታ

የመጀመሪያው ደረጃ የአጀንዳ ሀሳቦች ማሰባሰቢያ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎቸን የሚወክሉ ሰዎችን መለየት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ከየወረዳው ከተለዩ በቁጥር ከ8-10 የሚደርሱ የማህበረሰብ ክፍሎች ከእያንዳንዳቸው 10 ተሳታዎች እንዲለዩ ይደረጋል፡፡ በመጀመሪያው የኮሚሽኑ አካሄድ ከእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል የሚለየው ተሳታፊ በቁጥር 50 ነበር፡፡ ይህም የምክክር ሂደቱን ይበልጥ አሳታፊና አካታች ለማደረግ ታስቦ የተወሰነ የነበረ ቢሆንም በአፈጻጸም ሲታይ ግን አስቸጋሪ ሆኖ ተግኝቷል፡፡ በዚህ ስሌት ከ አንድ ወረዳ በአማካይ ከ400-500 ተሳፊዎች የሚኖሩ ሲሆን ይህን ያህል ሰው ለማሳተፍ የተደረገው ጥረት ከሎጀስቲክ፣ ከጊዜና ከሰው ሀይል አቅም አኳያ ፈታኝ ሆኖ በመገኘቱ የተሳታፊው ቁጥር ከአንድ ማህበረሰብ ክፍል ከ50-10 እንዲቀነስ ተወስኖ እየተሰራበት ነው፡፡ ይህ መሆኑ ግን ከእያንዳንዱ ወረዳ የአጀንዳ ሀሳቦችን እንዲሰጡ ወይም በምክክሩ ሂደት ላይ በሚሳተፉ ተዋካዮች ቁጥር ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ተሳታፊዎች እንዴት ይለያሉ?

ተሳታፊዎችን ከየወረዳው ለመለየት የሚደረገው ጥረት በተባባሪ አካላት እገዛ የሚከናወን ነው፡፡ በእያንዳንዱ ወረዳ በአማካይ ቁጥራቸው ከ 7-9 የሚደርስ ሰዎች በሂደቱ ይሳተፋሉ፡፡

ተባባሪ አካላቱ እነማን ናቸው?

በአብዛኞቹ ወረዳዎች በተባባሪነት የሚሳተፉ አካላት በዋናነት 7 ናቸው፡፡ እንደየ አከባቢው ሁኔታ ለሂደቱ ስኬት ጠቄማታቸው የተማነባቸው አካላት ሊካተቱ ይችላሉ፡፡

partners 02

ተባባሪ አካላት በምን መስፈርት ተመረጡ?

  • በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ ባላቸው አንጻራዊ ከፍተኛ ተቀባይነትና ገለልተኝነት ያላቸው መሆኑ፤
  • በአብዛኞቹ ክልሎች በወረዳ ደረጃ መሰረት ያላቸው መሆናቸው፤
  • የተቋማቱ ጥምረቶች ወይም ሀገር አቀፍ ማህበራቱ ስራውን ለማከናወን ፈቃደኛ ሆነው ከኮሚሽኑ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የፈረሙ መሆናቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ተባባሪ አካላት የመጀመሪያ ደረጃ ተሳታፊዎችን የሚለዩበት ሂደት

ተባባሪ አካላትን ኮሚሽኑ ባዘጋጀው መስፈርትና ተቋማቱ ከኮሚሽኑ ጋር በደረሱበት ስምምነት መሰረት የሚለዩትና ለኮሚሽኑ የሚያሳውቁት በሀገር አቀፍና በክልል ያሉ ማህበራት ወይም ጥምረቶች ናቸው፡፡ እነዚህም፡-

  • የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ፤
  • የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፤
  • የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፤
  • የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፤
  • የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የዕድሮች ማህበራት ጥምረት ናቸው፡፡

ከነዚህ በተጨማሪ ከፍርድ ቤት የሚወከሉ ዳኛና የወረዳ ተወካይ በሂደቱ እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ እዚህ ላይ አንዳንድ ወገኖች የወረዳ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት መወከል ላይ ከገለልተኝነት አኳያ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ለጥያቄያቸውም መሠረት የሚያደርጉት እንዚህ ተወካዮች በአመዛኙ የገዢው ፓርቲ አባላት የመሆን ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ ሂደቱ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ በሚል ነው፡፡ ነገር ግን የወረዳው ተወካይ እንዲካተት የሚደረገው መንግስት አንዱ የሂደቱ ባለድርሻ አካል እንደመሆኑ መጠን ተሳታፊ መሆን ስለሚገባውና የኮሚሽኑን ነጻነትና ገለልተኝትን በጠበቀ መልኩ ከመንግስት መደረግ ያለባቸውን ድጋፎች በሚፈለገው ልክ ማግኘት አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ሂደቱ ላይ ሁሉም ተባባሪ አከካላት እኩል ድምጽ ያላቸው በመሆኑ አንድ ድምጽ ያለው የወረዳ ተወካይ ሌሎቹ ተወካዮች በጥንካሬ እስከሰሩ ድረስ የሚያሳድረው የተለየ ጫና ይኖራል ተብሎ አይወሰድም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከወረዳ የተወከለው ሰው የግድ የወረዳ አስተዳዳሪ መሆን የሌለበት ከመሆኑም በላይ በኮሚቴ ውስጥ ሲካተትም መንግስትን እንጂ በሥልጣን ላይ ያለን የትኛውንም ፓርቲ ወክሎ ጉዳይ እንዲያስፈጽም አይደለም፡፡

በሌላም በኩል የፖቲካ ፓርቲዎችም ተሳትፎ በተመሳሳይ መልኩ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ በተባባሪነት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የሚወከል ሰው አባል የሆነበትን ፓርቲ ፍላጎት እንዲያስፈጽም አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የወከለው የጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ም/ቤት እንደመሆኑ መጠን በመርህ ደረጃ የም/ቤቱን ሁሉንም አባላት ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ይህ እንደተጠበቀም ሆኖ ም/ቤቱን የሚወክሉ ሰዎች በሚቻለው መጠን ሁሉ ከተለያዩ የፖቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ ስለመሆናቸውም ተገቢው ክትትል ይደረጋል፡፡

የተበባሪ አካላት ሥልጠና

ለተባባሪ አካላት የሶስት ቀናት ስልጠና ይሰጣል፡፡ ስልጠናው በዋናነት ስለሀገራዊ ምክክር ዓለም አቀፋዊ ጽንሰ ሀሳብ፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ምክክር መሰረታዊ ጉዳዮችና ሂደቱን ስለሚመራው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርኮሚሽን፣ በኮሚሽኑ የተዘጋጀው የተሳታፊዎች ልየታ ስነዘዴና ከየአከባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ በሚተገበርበት ሁኔታ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ከስልጠናው በተጨማሪም ለስራቸው የሚያስፈለጓቸው አስፈላጊ ቅጾች፣ ደብዳቤዎችና ሌሎች ተያያዥ ግብአቶችን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ሰብሳቢና ጸሃፊም እንዲሰይሙ ይደረጋል፡፡

partner training sidama

partner training addisababa

የተባባሪ አካላት ስልጠና – ሲዳማ ክልል

የተባባሪ አካላት ስልጠና – አዲስ አበባ

ተሳታፊዎችን ከወረዳ መለየት

ተባባሪ አካላቱ ከስልጠናው በኋላ ወደየወረዳቸው በመመለስ ስራውን ማከናወን በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ምክክርና የስራ ክፍፍል አድርገው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይገባሉ፡፡ በተቋም ወይም በማህበር ተወከለው ለሚሳተፉ የማህበረሰብ ክፍሎች ለምሳሌ እንደ መምህራን ማህበር፣ እድር ለመሳሰሉት በኮሚሽኑ የተዘጋጀውን ደብዳቤ በማድረስና ተገቢውን ክትትል በማድረግ ተቋማቱ ወይም ማህበራቱ በደብዳቤ እንዲወክሉ ያደርጋሉ፡፡

በተቋም ወይም በማህበር የማይወከሉትን ወይም በከፊል ተወከለው የተቀረውን ደግሞ ተባባሪ አካላቱ የሚለያቸውን የህበረተሰብ ክፍሎች በኮሚሽኑ በተሰጣቸው መስፈርት መሠረት ይለያሉ፡፡ ተሳታፊዎች የሚለዩበት መስፈርቶች ከተቋም ወይም ከማህበር ሲወከሉም ሆነ በተባባሪ አካላቱ ሲለዩ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ከሥልጠናው በተጨማሪ ኮሚሽኑ ባለሙዎችን በመመደብ ተባባሪ አካላቱ በአግባቡ እየሰሩ መሆናቸውን ይከታተላል፡፡ ችግሮች ሲኖሩም ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግ ያደርጋል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ለመሳተፍ መሰረታዊ መስፈርቶቹ ምንድናቸው?

criterias

በተቋም ወይም በማህበርም ሆነ በተባባሪ አካላቱ የተለዩ ተሳታፊዎች የተለዩት ኮሚሽኑ ያስቀመጠውን የአሰራር ስርአትና ሂደት ተከትሎ ስለመሆኑ የተባባሪ አባላቱ ኮሚቴ በፊርማቸው በማረጋገጥና በተሰጣቸው ቅጽ ላይ በመሙላት ለኮሚሽነኑ ያስረክባሉ፡፡

ኮሚሽኑም ተገቢውን ማጣራት በማድረግና በማረጋገጥ ሰነዶችን ይረከባል፡፡

በመጀመሪያው ደረጃ በተባባሪ አካላቱ እገዛ ከየማህበረሰብ ክፍሉ የተለዩት 10 ተሳታፊዎች አመቺ ወደ ሆኑ የዞን ከተሞች እንዲሰባሰቡ ይደረጋል፡፡ የትራንስፖርትና የሎጀስቲክ አቅርቦቶች አስቸጋሪ በሆነባቸው እንደ አፋር ባሉ ክሎሎች ተሳታፊዎችን ወደ አማካይ ከተሞች ማሰባሰብ ሳይቻል ሲቀር በየወረዳቸው ማከናወን የግድ ብሏል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ተሳታፊዎች በቀጣይ የሚያከናውኑት ተግባር ኮሚሽኑ በክልል ደረጃ በሚያዘጋጃቸው መድረኮች ላይ ወረዳቸውን በመወከል የአጀንዳ ሀሳቦችን የሚሰጡ ተወካዮችን መምረጥ ነው፡፡

አጠቃላይ ሂደቱ አንድ ሙሉ ቀን ይካሄዳል፡፡ በግማሹ ቀን ለተሳፊዎች ስለ ምክክር ምንነትና በተለይም በኢትዮጵያ ያለውን አስፈላጊነትና ፋይዳ እንዲሁም ተወካዮቻቸውን ለምን እንደሚመርጡና የአመራረጥ ሂደቱን በተመለከተ ገለጻ ይደረግላቸዋል፡፡ ገለጻውን መሰረት በማድረግ ጥያቄዎች ወይም ሀሳብ ካላቸው እንዲያቀርቡ ዕድል ይሰጣል፡፡ ለቀረቡ ጥቄዎች ተጨማሪ ማብራሪ ከተሰጠ በኋላ ከሰአት በኋላ ባለው ጊዜ ወደ ውክልና ሂደቱ ያልፋሉ፡፡

tesatafi 01

አጠቃላይ ከገለጻውን ከትሎ ከሰአት በኋላ እያንዳንዱ ማህበረሰብ በአብዛኛው በትምህርት ቤቶች በሚዘጋጁ ክፍሎች በየወከለው ማህበረሰብ እንዲሰባሰብ ይደረጋል፡፡ የመማሪያ ክፍሎች እጥረት በሚጋጥመበት ወቅት የዛፍ ጥላዎችን እንዲሁም የመሰብሰቢ አዳራሾችን በመከፋፋል የውክልና ሂደቱ ይከናወናል፡፡

tesatafi 02

በመጀመሪው አጠቃላይ መድረኩ ላይ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች ካሉ በየማህበረሰቡ በመዘዋወር ተጨማሪ ገለጻና በኮሚሽኑ የተዘጋጀውን የቃለ ጉባኤ ቅጽ አሞላልን በተመለከተ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡

እንዳንዱ ማህበረሰብ የውክልና ሂደቱን የሚስተባብሩለት አንድ ሰብሳቢና ጸሀፊ እንዲመርጥ ይደረጋል፡፡ በሰብሳቢነት ወይም በጸሀፊነት የሚመረጡ ሰዎች በውክልና ሂደቱ እንዲሳተፉ በማህበረሰቡ ከተጠቆሙ የመወዳደር መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ሂደቱን የማስተባበርና ቃለ ጉባኤ የመያዝ ሀላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡

የውክልና ሂደቱ የሚከናወነው ሙሉ በሙሉ በማህበረሰቡ ሲሆን የኮሚሽኑ ባለሙዎችም ሆኖ ተባባሪ አካላት በሂደቱ ጣልቃ አይገቡም፡፡ በሂደቱ ላይ አለመግባባቶች ከተፈጠሩ ብቻ ለተፈጠረው አለመግባባት እልባት ለመስጠትና ሂደቱ እንዲቀጥል ለማድረግ ብቻ ጣልቃ ሊገቡ ይችላሉ፡፡

የውክልና ሂደቱ በአብዛኛው የሚካሄደው ዲሞክራሲዊ አካሄዶችን ተከትሎ ነው፡፡ መጀመሪያ ጥቆማዎች ይቀርባሉ፡፡ የሚጠቆሙ ሰዎች እስከ 5 ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ተሳታፊዎቹ ለተጠቆሙት ሰዎች ድምጽ ይሰጣሉ፡፡ድምጽ አሰጣጡ እንደ ማህበረሰቡ ፍላጎትና ስምምነት እጅ በማውጣት ወይም በወረቀት በሚስጥር በሚሰጥ ድምጽ ሊሆን ይችላል፡፡ የተሰጡ ድምጾች ተቆጥረው ከፍተኛ ድምጽ ያገኙ ሁለት ተጠቋሚዎች የሚወከሉ ሲሆን 3ኛ የወጣው/ችው በተጠባባቂነት ይይዛሉ፡፡ ውስን የህዝብ ቁጥር ባላቸው ክልሎች ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖር ለማድረግ ሲባል ተወካዮቹ በቁጥር 4 የሚሆንባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡

የውክልና ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ተሳታፊዎች ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የቃለ ጉባኤ ቅጽ ላይ ስምና ፊርማቸውን አኑረው ሂደቱ ይጠናቀቃል፡፡ ኮሚሽኑም ሁሉንም ሰነዶች በአግባቡ እንዲሰበሰቡ እንዲሰነዱ ያደርጋል፡፡

endc documentation

የኮሚሽኑ ዶክመንቴሽን በከፊል

የክልል እና የከተማ አስተደደር ተሳታፊዎች ልየታ

በሂደትና እንደየአከባቢው ሁኔታ የሚጨመሩ ወይም የሚቀነሱ መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ኮሚሽኑ የሚከተሉት አካላት በወኪሎቻቸው አማካኝነት በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ለይቷል፡፡ አብዛኞቹ ተቋማትና ማህበራት እንደመሆናቸው መጠን በአብዛኛው የኮሚሽኑን መስፈርት መሠረት በማድረግ በደብዳቤ የሚወከሉ ናቸው፡፡ ይህ አንደተጠበቀ ሆኖ ባላቸው ተቀባይነትነ ተጽእኖ ፈጣሪነት እንዲሁም በሂደቱ መሳተፋቸው አዎንታዊ ፋይዳ አለው ብሎ ኮሚሽኑ ያመነባቸውን ግለሰቦች  እንዲካተቱ የማድረግ አካሄድን ይከተላል፡፡

የክልል እና የከተማ አስተደደር ተሳታፊዎች

የክልል እና የከተማ አስተደደር ተሳታፊዎች

በፌደራል ደረጃ የሚወከሉ ተሳታፊዎች

በፌደራል ደረጃ የሚወከሉ ተሳታፊዎች ከሞላ ጎደል በክልልና ከተማ አስተዳደር ያለውን የውክልና ሂደት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

በፌደራል ደረጃ የሚወከሉ ተሳታፊዎች

የዲያስፖራ ተሳታፊዎች

ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ወገኖች ሁሉን አካታችና አሳታፊ በሆነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት ተሳታፊ ናቸው፡፡ አብዛኛው የዲስፖራው ማህበረሰብ ለሀገሩ ቀናኢና በሚችለው አቅም የተሻለች ሀገር ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት ገንቢ አስተዋጽኦ የሚያበርክት ቢሆንም በመሠረታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያሉ የሀሳብ ልዩነቶች ወይም አለመግባባቶች እንዳሉበት ይተወቃል፡፡ በመሆኑም በምክክር ሂደቱ ተሳታፊ መሆኑ ለሂደቱ ስኬታማናትና ለሚደረስባቸው መግባባቶች የራሱ አስተዋጽኦ አለው ተብሎ ይታመናል፡፡

በዚሁም መሠረት ዲያስፖራው ማህበረሰብ  በምን መልኩ ቢሳተፍ ይበልጥ ተካታች ሊሆን እንደሚችል በሀገር ውስጥ ካሉና በውጭ ከሚኖሩ የማህበረሰቡ አባላት ጋር ሰፊ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ የሚገኙ ግብአቶችን በማሰባሰብ ሂደቱ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡

የዲያስፖራ ተሳታፊዎች