የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ ከግንቦት 21 ጀምሮ ላለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት ሲያስተባብር የነበረውን ክንውን ጨርሷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወኪሎች በአጀንዳ ሀሳቦች ላይ ሲያደርጉት የነበረው ውይይት እና ልየታ ዛሬ መቋጫውን አግኝቷል፡፡
የከተማዋን ነዋሪ በተለያዩ ቡድኖች ወክለው የተገኙ ከ2000 በላይ ተወካዮች ከወከላቸው የሕብረተሰብ ክፍል በአደራ በተቀበሏቸው የአጀንዳ ሀሳቦች ላይ ላለፉት ሶስት ቀናት ከተወያዩ በኋላ በከተማ አስተዳደር ደረጃ በሚካሄደው ምክክር እንዲንፀባረቁላቸው የፈለጓቸውን አጀንዳዎች ለይተው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
በሂደቱ ሲሳተፉ የነበሩት የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች የጋራ የሚሏቸውን አጀንዳዎች ለይተው ካደራጁ በኋላ የአጀንዳዎቹን ሀሳቦች በከተማ አስተዳደር ደረጃ በሚካሄደው ምክክር ላይ የሚያቀርቡላቸውን በአጠቃላይ 121 ተወካዮቻቸውን መርጠዋል፡፡የተወካዮቹ ምርጫ በሚስጥር የተከናወነ ሲሆን ተሳታፊዎች በነፃነት እና በሚስጥራዊ ሁኔታ የሚፈልጉትን እጩ መርጠዋል፡፡
ኮሚሽኑ በዚህ ከተማ አቀፍ የምክክር ምዕራፍ ሌሎች ባለድርሻ የሂደቱ ከዋኞች እንዲሆኑ ያደረገ ሲሆን እነሱም የፓለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ማህበራት ተወካዮች ፣ የሶስቱ የመንግስት አካላት ተወካዮች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ናቸው፡፡
እነዚህ ባለድርሻ አካላት ዛሬ ግንቦት 23/2016 ዓ.ም በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ በተካሄደው መርሃግብር ለምክክሩ የሚያግዛቸው ገለፃ እንደተደረገላቸው መዘጋበችን አይዘነጋም፡፡
ከላይ የተጠቀሱ ባለድርሻ አካላት በጋራ ከነገ ግንቦት 24/2016 ዓ.ም ጀምሮ በሚኖሩ ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ አጀንዳዎች ተወያይተው አጀንዳቸውን ያደራጃሉ፡፡
በመጨረሻም አዲስ አበባ ከተማን የሚወክሉ እና በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮቻቸውን ከመሀከላቸው የሚመርጡ ይሆናል፡፡