የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አጀንዳ ተረከበ

ሚያዚያ 29/2017 ዓ.ሞ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ያደራጃቸውን ሀገራዊ አጀንዳዎች በዛሬው ዕለት ተረክቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ ፌዴሬሽኑ የሴቶችን አጀንዳዎች በልዩ ሁኔታ አደራጅቶ በማስረከቡ በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል፡፡

የሴቶችን መብቶች ለማስከበር ብዙ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ከኮሚሽኑ ጋር በመተባበር ሲሠራ መቆየቱን አመላክተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት 30 በመቶ ሴቶች እንዲሳተፉ የሚያደርግ ስነዘዴን በመከተል፤ በርካታ ሴቶችን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ አሳትፏል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ፌዴሬሽኑ ከኮሚሽኑ ጋር የጀመረውን የጋራ ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ዋና ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመርሐግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አስካል ለማ፤ ፌዴሬሽኑ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ በትብብር ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

አጀንዳዎቹ በሁሉም ዘርፍ ያሉ የሴቶችን ጉዳዮች በማካተት ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በትብብር መዘጋጀቱንም ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል፡፡

የሴቶችን መብቶችና ተጠቃሚነት የተመለከቱ 8 አበይት ክፍሎችና 25 ዝርዝር አጀንዳዎች በሰነድ መዘጋጀታቸውንም አብራርተዋል፡፡

በመድረኩ ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተገኙ የስራ ኃላፊዎችና መገናኛ ብዙኃን ተገኝተዋል፡፡