የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቤንሻንጉል ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮችን ከጥቅምት 02 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ከየማህበረሰብ ክፍሉ እንዲመረጡ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ሂደቱም በሁለት ዙር የሚከናወን ሲሆን በመጀመሪያው ዙር 13 የአሶሳ ዞን ወረዳዎች የሚካተቱበት መርሃ ግብር ይካሄዳል፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላም 14 ወረዳዎች የሚሳተፉበት ሁለተኛው መርሃ ግብር ይካሄዳል፡፡
በክልሉ በአጠቃላይ የ22 ወረዳዎችና የአምስት ከተማ መስተዳድር የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የሚካሄደው የተወካዮች መረጣ በድምሩ 2700 የሚሆኑ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮችን ያሳትፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህም ሂደት ከእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል አስር አስር ሰዎች የሂደቱ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
በዛሬው ዕለት እየተካሄደ በሚገኘው የተወካዮች መረጣ ከአሶሳ ከተማ ወረዳ 1 እና 2፣ አብራሞ ወረዳ እና ኡራ ወረዳ በአጠቃላይ 360 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ለተሳታፊዎች ስለምክክር ፅንሰ ሀሳብ፣ ኮሚሽኑ እስካሁን ስላከናወናቸው ተግባራት፣ ሰለሀገራዊ ምክክር ሂደቶች በኮሚሽኑ ባለሙያ ገለፃ በመደረግ ላይ ነው፡፡ ከሰዓት በኋላ በሚቀጥለው መርሃ ግብርም ተሳታፊዎች ለአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ይወክሉናል የሚሏቸውን ሁለት ሁለት ግለሰቦችን ከአንድ ተጠባባቂ ጋር በየወረዳቸው እና በየማህበረሰብ ክፍሎቻቸው ይመርጣሉ፡፡