ኮሚሽኑ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በማረቆ ልዩ ወረዳ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮችን ዛሬ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ከየማህበረሰብ ክፍሉ እንዲመረጡ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በቆሼ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ መርሐ-ግብር የአንድ ቀን መርሐ-ግብር ሲሆን ከ90 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎችን የሂደቱ አካል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ በሌሎች አካባቢዎች ሲደረግ እንደነበረው ተሳታፊዎች ስለሀገራዊ ምክክር እና ተያያዥ ጉዳዮች ግንዛቤን ይጨብጡ ዘንድ ስለምክክር ፅንሰ ሀሳብ፣ ኮሚሽኑ እስካሁን ስላከናወናቸው ተግባራት፣ ሰለሀገራዊ ምክክር ሂደቶች እና ተሳታፊዎች ተወካዮቻቸውን ሲመርጡ ሊከተሏቸው ስለሚገቡ ሂደቶች ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ ያንን ተከትሎም ውይይት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ በመቀጠልም ተሳታፊዎች ለአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ይወክሉናል የሚሏቸውን ሁለት ሁለት ግለሰቦች ከአንድ ተጠባባቂ ጋር በየወረዳቸው እና በየማህበረሰብ ክፍሎቻቸው ይመርጣሉ፡፡