ሀገራዊ ምክክር የሰብዓዊ መብቶችን ከማጎልበት አንፃር የሚኖረው ሚና
18/4/2017
ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ ለተፈጠሩ የውስጥ ችግሮች መፍትሔን ለማበጀት የሚሰራ ፓለቲካዊ ሂደት ነው፡፡
ሂደቱ በተለያዩ ደረጃዎች ሊገለፁ የሚችሉ ቀጥተኛ ውጤቶች አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል የሕገ-መንግስት ማሻሻያዎች፣ የፖለቲካ ስርዓት ማሻሻያዎች፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች፣ የሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎች እና ቀደም ሲል ለተፈፀሙ በደሎች መፍትሔን ማበጀት እንደ ተጠባቂ ውጤት ሊመዘገቡ ይችላሉ፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው የሰብዓዊ መብቶች መከበር የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በአዎንታዊ መንገድ ሊደግፋቸው ከሚችላቸው ውጤቶች አንዱ ነው፡፡ ይህም የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች እና የሰብዓዊ መብቶች ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው አመላካች ሲሆን ከዚህ በታች የተገለፁት ሀሳቦች የሁለቱን ግንኙነት ያስረዳሉ፡፡
- አካታችነት እና ከአድሎ የፀዳ መሆን
የሀገራዊ ምክክር ሂደት እና የሰብዓዊ መብቶች ሁሉም ዜጎች በውሳኔ ሰጪነት ሂደቶች ላይ በእኩልነት ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከአድሎ የፀዱ እንዲሆኑ ይደነግጋሉ፡፡ የሀገራዊ ምክክር ሂደትም ዜጎችን በፆታ፣ በቀለም፣ በጎሳ፣ በሐይማኖት እና በሌሎች ማሕበራዊ መገለጫዎች በእኩልነት የሚያይ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ነው፡፡ ይህም እያንዳንዱ ዜጋ በሂደቱ በእኩልነት እንዲታይ መደላድልን ይፈጥራል፡፡
- አሳታፊነት እና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ማረጋገጥ
የሰብዓዊ መብቶች ሁሉም ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት መግለፅ እንደሚችሉ ይደነግጋሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የውሳኔ ሰጪነት ሚናውን እንዲጫወት መንገዱን ያመቻቻሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በትይይዩ የሀገራዊ ምክከር ሂደቶችም ዜጎች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲያንሸራሽሩ ከማስቻሉም በላይ የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውንም ያጎላዋል፡፡
- ፍትሕ እና ተጠያቂነትን ማስፈን
የሰብዓዊ መብቶች በተለያየ ረገድ ፍትሕን ለተነፈጉ እና ድምፃቸው ላልተሰማ ወገኖች ፍትሕን እንዲያገኙ ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይህ ማለት አግባብነት ያለው የተጠያቂነት ስርዓት በፍትሕ ስርዓት ውስጥ እንዲኖር መንገዱን በማመቻቸት ለዲሞክራሲያዊ ልምምዶች በር ይከፍታል፡፡ ከዚህ ጋር በትይዩ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ሊያሳኩ ከሚያልሟቸው ውጤቶች አንዱ በሰብዓዊ መብት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ማድረግ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
- ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን
የሰብዓዊ መብቶች ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ በእኩል ተሳትፎን በማድረግ ተጠቃሚ ሆኖ የተሻለ የትምህርት፣ የጤና፣ የስራ እንዲሁም የሀብት ክፍፍል እንዲኖረው መብት ይሰጣሉ፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደቶችም ዜጎች በእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ በጋራ ለማበጀት ይወያያሉ፤ የመፍትሔ ሀሳቦችንም ያመነጫሉ፡፡
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!