የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ፅናት ለኢትዮጵያ ማህበር ከሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ (ዲሲ ግብረ ሀይል) ጋር በመቀናጀት “በምክክር ሀገር ትዳን” የሚል ዘመቻ በማስተባበር ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ፡፡

image (1)

ማህበሩ “በምክክር ትዳን ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ ትላንት መጋቢት 26/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡

የፅናት ኢትዮጵያ ማህበር አባል አቶ ፋሲል አጥሌ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካላት የሚስተዋሉ አለመግባባቶች ወደ ግጭት እየተሸጋገረ የሀገር አንድነት እና ህልውና እየፈተነ ቆይቷል፣ ዛሬም በመፈተን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ግጭቱና አለመግባባቱ ወደ ብሔራዊ ቀውስ ከመግባቱ በፊት ሩቅ ሆኖ ከመብሰልሰል “በምክክር ትዳን ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ የንቅናቄ ዘመቻ በማድረግ በኢትዮጵያ በሂደት ላይ ላለው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የበኩላቸውን አስተዎጽኦ ለማበርከት እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

የዛሬው ፓናል ውይይትም የዚሁ እንቅስቃሴ አንዱ አካል መሆኑንም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ኮሚሽኑ በተለይም ምክክሩ ሁሉን አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ኮሚሽኑ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ገለፃ አቅርበዋል፡፡

ከአካታችነትና አሳታፊነት አንፃር ለዲያስፖራው ማህበረሰብ ትኩረት በመስጠት በሂደቱ እንዲሳተፍ ጭምር እየተደረገ መሆኑን በማብራሪያቸው አመላክተዋል፡፡

በቅርቡ የአጀንዳ ግብአቶችን የማሰባሰቢያ ህዝባዊ መድረኮችን ለማስጀመር ኮሚሽኑ ቅድመ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ሁሉም የበኩሉን አስተዎጽኦ ማበርከት እንዳለበት የገለፁት አቶ ጥበቡ መድረኩን ያዘጋጁትን ጽናት ለኢትዮጵያ ማህበር እና ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበርን በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል፡፡

“በምክክር ትዳን ሀገር” የፓናል ውይይት መርሀ-ግብር ላይ በያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፣ በዮናስ አሸኔ (ዶ/ር) እንዲሁም በወ/ሮ መሠረት ተጫኔ ምክክርን የተመለከቱ የጥናት ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

image (1)