የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን 35 አባላትን ያቀፈ የአማካሪ ኮሚቴን ማቋቋሙን ይፋ አድርጓል

347616663 203053149226458 8082203242027921711 n

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን 35 አባላትን ያቀፈ የአማካሪ ኮሚቴን ማቋቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን የገለፀው ዛሬ ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም ከኮሚቴው አባላት ጋር ለመተዋወቅ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ሲሆን ከአባላቱም ጋር ገንቢ ውይይትን አድርጓል፡፡ ኮሚሽኑ በኮሚቴው እንዲካተቱ የጋበዛቸው ግለሰቦች በተለያየ መልኩ ለኮሚሽኑ ስራዎች ድጋፎችን የሚያደርጉ ሲሆን በተለያየ ልምድ እና ሙያ ውስጥ እንዳሉም ተገልጿል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ምሁራን እንዲሁም በምክክር ሂደት ላይ ስራዎችን ያከናወኑ ግለሰቦች እና የተቋማት ተወካዮች የኮሚቴው አባላት ሆነው መካተታቸው ነው፡፡

ኮሚሽኑ ይህንን ኮሚቴ ሲያቋቋም በተቋቋመበት አዋጅ 1265/2014 ላይ ያሉ የህግ ማዕቀፎችን መሰረት አድርጎ ሲሆን ለኮሚቴውም ስራዎችን የሚያከናውንበትን የውስጥ መመሪያ አዘጋጅቶለታል፡፡ በዚህም መሰረት የተቋቋመው ኮሚቴ ኮሚሽኑ በአዋጅ እንዲሰራ የተሰጠውን ተግባራትና ሀላፊነቶች በአግባቡ እንዲወጣ ኮሚሽኑን በተለያዩ ዘርፎች በማማከር እገዛን ያደርጋል፡፡

በተዘጋጀው የትውውቅ መርሃ ግብር ላይ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በኮሚሽኑ የተከናወኑ አንኳር ተግባራትን እና በቀጣይ ሊሰሩ የታቀዱ ስራዎችን በተመለከተ ለኮሚቴው አባላት ገለፃን አድርገዋል፡፡ ከተደረገው ገለፃና ማብራርያ ቀጥሎም በግብአትነት የሚወሰዱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የተሰነዘሩ ሲሆን ለቀረቡት ጥያቄዎችም መልሶችና እና ማብራሪያዎች በኮሚሽኑ አባላት ተሰጥተዋል፡፡