የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሻሸመኔ ክላስተር በሚገኙ ስድስት ዞኖች በወረዳና ከተማ አስተዳደር ደረጃ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት አስጀመረ፡፡

436235046 421359473918821 6427262530941620310 n

በመክፈቻ መርሀግብሩ ላይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) እና አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ተገኝተዋል።

ኮሚሽነር አምባዬ በመክፈቻ ንግግራቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተሳታፊዎች የተወከሉበትን የማኅበረሰብ ክፍል አውድ በተመለከተ በቂ ግንዛቤ ያዳበሩ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን ገልፀዋል።

ገለልተኛ ተቋማትና አጋሮችን በማሳተፍ ሥራዎችን ማከናወኑንና ወደፊትም እንደሚያከናውንም አብራርተዋል፡፡

ኮሚሽነር ዮናስ በበኩላቸው ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ለሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ለተሳታፊዎችና ለተባባሪ አካላት ሂደቱ በክልሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለነበራቸው ከፍተኛ ሚና በኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ተሳታፊዎች የሀገራዊ ምክክር ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም የአመራረጥ ሂደቱን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ማብራሪያ እየተደረገላቸው ነው፡፡

በሻሸመኔ ከተማ ዛሬ ሚያዚያ 05/2016 ዓ.ም የተጀመረው በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተወካዮችን የማስመረጥ ሂደት እስከ መጪው አርብ ሚያዚያ 11/2016 ዓ.ም በተመሳሳይ ይካሄዳል፡፡

በሻሸመኔ ክላስተር ውስጥ የተካተቱ ዞኖች ስድስት ሲሆኑ እነርሱም ባሌ፣ምስራቅ ባሌ፣ ቦረና፣ ምስራቅ ቦረና፣ ጉጂ እና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች ናቸው፡፡

እስከ አርብ ሚያዚያ 11/2015 ዓ.ም በሚኖረው ሂደት ከስልሳ ስድስት (66) ወረዳዎች የመጡ 5ሺ 280 የህብረተሰብ ወኪሎች በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን ይመርጣሉ፡፡

በዛሬው እለት ከ11 ወረዳዎች የመጡ 880 የህብረተሰብ ወኪሎች ተወካዮቻቸውን እያስመረጡ ይገኛሉ::

436235046 421359473918821 6427262530941620310 n