የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአጀንዳ አሰባሰብ አሰራር ስርዓቱ የሚያግዙ ግብዓቶችን ከባለድርሻ አካላት ሰበሰበ፡፡

addis ababa 1.

ኮሚሽኑ በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ለሚያካሂደው አጀንዳ የማሰብሰብ ተግባር ያዘጋጀውን ረቂቅ የአሰራር ስርዓት በሚመለከተታቸው ባለድርሻ አካላት አስተችቶ ግብዓቶችን ሰብስቧል፡፡

በአዲስ አበባ ሀይሌ ግራንድ ሆቴል በተዘጋጀው በዚህ መርሐ-ግብር ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ከ250 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዲሁም ከመንግስት እና ከሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተወከሉ በመድረኩ ተሳትፈዋል፡፡

በመርሐ-ግብሩ ላይ ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን አበይት ተግባራት እንዲሁም የአጀንዳ አሰባሰብ የአሰራር ስርዓቱን በተመለከተ በኮሚሽኑ  ምክር ቤት አባላት  ገለጻ እና ማብራሪያ ተደርጓል፡፡

በቀረበው የአሰራር ስርዓት ላይ ኮሚሽኑ የገለልተኝነት፣ አሳታፊነትና አካታችነት መርሆዎችን ተከትሎ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ በሚሰበስብባቸው ሁኔታዎች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የቀረበውን ገለፃ መነሻ ያደረጉ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን በመሰንዘር ኮሚሽኑ ያዘጋጀውን ሰነድ ሊያጎለብቱ የሚችሉ ሀሳቦችን አንሸራሽረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአማራና ትግራይ ክልሎች ውጪ ባሉ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በወረዳ ደረጃ ሲያከናውን የቆየውን የተሳፊዎች ልየታ ስራ በተሳካ ሁኔታ ስለማካሄዱም በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የተሳታፊዎች ልየታ በተጠናቀቀባቸው ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባሩን በቅርቡ ማከናወን እንደሚጀምርም ተጠቁሟል፡፡