የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የትግራይ ክልል ህዝብ ጥያቄዎችን እንረዳለን፤ዋጋም እንሰጣለን-ኮሚሽኑ

img 20251022 173843 529

የትግራይ ክልል ህዝብ ጥያቄዎችን እንረዳለን፤ዋጋም እንሰጣለን-ኮሚሽኑ

ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ከሚገኙ የሚድያ ባለሙያዎች ጋር ለሁለት ቀናት ያካሄደው የመጀመሪያው ዙር የውይይት መድረክ ተጠናቋል፡፡

በዚህ መድረክ ተገኝተው ስለ ኮሚሽኑ የስራ እንቅስቃሴ ማብራሪያ የሰጡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕሮፌሰር) ኮሚሽኑ በ11 ክልሎች፣ በሁለት ከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም በፌደራል ተቋማትና በዳያስፖራው ማህበረሰብ አካባቢዎች አጀንዳ አሰባስቦ ማጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡

የኮሚሽኑ የቀጣይ ዋና ትኩረት የትግራይ ክልል መሆኑን ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ ያለ ትግራይ ክልል ተሳትፎ ምክክር አካሄድን ማለት ስለማይቻል ለተግባራዊነቱ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ ምክክር ይሳካ ዘንድ የሚድያ ባለሙያዎች ለህብረሰተቡ ግንዛቤ በመፍጠር በሙያቸው እንዲያግዙም ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር የውይይት መድረክ የተሳተፉ የሚድያ ባለሙዎች በሰጡት አስተያየት ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ምክክር ለማድረግ በቅድሚያ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የተቀመጡ ተግባራት መፈፀም እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

ባለሙያዎቹ በመጠለያ ያሉ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ይመለሱ፣ የትግራይ ክልል ግዛቶች ይከበሩ የሚሉና ሎሎች በክልሉ ህዝብ ህልውና ላይ ተጋርጠዋል ያሏቸውን የህልውና ችግሮች አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በቀጥታ እነዚህን ጥያቄዎች የመመለስ ስልጣን የሌለው መሆኑን እንደሚገነዘቡ የገለፁት የሚድያ ባለሙያዎቹ በመንግስት ላይ ግፊት በማድረግ ግን ችግሮች እንዲፈቱ ሚና መጫወት ይችላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር) የትግራይ ክልል ሁኔታ በተለየ መልኩ መስተናገድ እንዳለበት እንረዳለን ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር ችግር ውስጥ ነን ያሉት ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ ትግራይ ክልል ግን በተለየ ችግር ውስጥ ስለመሆኑ ኮሚሽኑ እንደሚረዳም አክለዋል፡፡

ለሁሉም ችግር መነጋገር መፍትሄ እንደሆነ እናምናለን ያሉት ኮሚሽነሩ የሚድያ ባለሙያዎች መነጋገር የሚቻልበትን ድልድይ በመፍጠር ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች እንረዳለን፣ ዋጋም እንሰጣለን ሲሉም ኮሚሽር አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በማንኛውም አጋጣሚ የክልሉ ህዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በማንሳት ምክክሩን ማካሄድ የሚቻልበት አውድ እንዲፈጠር እየሰራን ነው፤ ይህንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አፅኦት ሰጥተውበታል፡፡

ጥቅት 12 እና 13/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የግልና የዲጂታል መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዲሁም የማህበረሰብ አንቂና በጎ ተፅኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተሳትፈዋል፡፡

ሁለተኛው ዙር ውይይት ነገ ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል።