የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የህብረተሰብ ወኪሎች ምክክር በስኬት ተጠናቀቀ

ggg

የህብረተሰብ ወኪሎች ምክክር በስኬት ተጠናቀቀ

ሚያዚያ 1/2017 ዓ.ም

በአማራ ክልል የምክክር ሂደት የህብረተሰብ ወኪሎች የምክክር መድረክ በስኬት መጠናቀቁን የክልሉ አስተባባሪ ኮሚሽነሮች አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ የምክክር ሂደት አስባባሪ ኮሚሽነሮች ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያምና ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ ላለፉት አምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የህብረተሰብ ወኪሎች ምክክር መጠናቀቁን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽር መላኩ ወ/ማርያም በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ባለፉት አምስት ቀናት በተካሄደው የህብረተሰብ ወኪሎች ምክክር ከክልሉ 263 ወረዳዎች የመጡ ከ4ሺ 500 በላይ ወኪሎች ተሳትፈዋል፡፡

ሂደቱ አሳታፊ፣ አካታችና ግልፅ በሆነ ሁኔታ ተካሂዶ መጠናቀቁንም ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም አረጋግጠዋል፡፡

ተሳታፊዎች ለክልላቸውና ለሀገራቸው ጠቃሚ የሆኑ እጅግ መሰረታዊ ሃሳቦችን በውይይት አዳብረው መለየታቸውንም በነበረን ክትትልና ድጋፍ ተመልክተናል ሲሉም አክለዋል፡፡

ኮሚሽር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው በአማራ ክልል የተካሄደው የማህበረሰብ ወኪሎች የምክክር ሂደት በኮሚሽኑ እቅድ መሰረት በውጤት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

በምክክሩ እንዲገኙ የተለዩ የህብረተሰብ ወኪሎች በሙሉ መገኘታቸውንና ነፃ፣ ገለልተኛና አሳታፊ በሆነ መልኩ ሃሳቦቻቸውን በውይይት ለይተው ለተመረጡ ወኪሎቻቸው ማስረከባቸውንም አክለዋል፡፡

የአማራ ክልል የምክክር ሂደት በህዝብና በመንግስት፣ በህዝብና በህዝብ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን መመካከርን ባህል በማድረግ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ከመጋቢት 27 እስከ ዛሬ ሚያዚያ 1/2017 ዓ.ም ሲመካካሩ የቆዩት የህብረተሰብ ወኪሎች በባለድርሻ አካላት ምክክርና በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ 270 ወኪሎችን መርጠውና ያጠናቀሯቸውን አጀንዳዎች በአደራ አስረክበው ሂደቱ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡