የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ተባባሪ አካላት እና ሚናቸው

collaborators. design

የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ተባባሪ አካላት እና ሚናቸው

 

ጥር 28/2017 ዓ.ም

 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በየወረዳው ባከናወናቸው የተሳታፊዎች ልየታ የሚያግዙትን ተባባሪ አካላት ለይቶ የመግባቢያ ስምምነት ሚያዚያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም መፈራረሙ የሚታወስ ነው።

 

ኮሚሽኑ ይህንን የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመው ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋሟት ጉባኤ፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እና ከኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የእድሮች ማህበራት ጥምረት ጋር ነው።

 

ኮሚሽኑ ለዚህ ስራ መሳካት እነዚህን አካላት ሲመርጥ የተለያዩ መስፈርቶችን እንደ ቅድመ ሁኔታ ቢያስቀምጥም ልዩ ትኩረት የሰጠው ግን የአካላቱ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን የመቋቋም ብቃት እንደሆነ ይታወሳል።

 

ከዚህ ባሻገር ኮሚሽኑ በስራው ላይ ሊገጥሙ የሚችሉ የፀጥታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመከላከል የወረዳ አስተዳዳሪዎችን እና የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች የሂደቱ አካል እንዲሁኑ በአሰራር ስርዓቱ ደንግጎ ውጤታማ የሆነ የተሳታፊዎች ልየታን በእነዚህ ተባባሪ አካላት ታግዞ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

 

ሆኖም ግን ኮሚሽኑ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እና ዓውድ ላይ ተመስርቶ ከላይ ከተጠቀሱት ተባባሪ አካላት በተጨማሪ ሂደቱን ማህበረሰቡ እምነት የሚጥልባቸውን ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት በተባባሪ አካልነት በማቀፍ አካሂዷል፡፡ በዚህ መሰረት፦

 

  1. በአፋር ክልል
  • የጎሳ መሪዎች
  • የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች
  • የሼሪያ ፍርድ ቤት ዳኞች (ቃዲዎች)
  • የሀገር ሽማግሌዎች (ሱልጣኔቶች)፤

 

  1. በሶማሌ ክልል
  • የጎሳ መሪዎችን/የሀገር ሽማግሌዎችን/ ኡጋዞች
  • የሸርያ ፍርድ ቤት ዳኞች
  • ጀምአዎች (የሴቶች አደረጃጀቶች) ፤

 

  1. ኦሮሚያ ክልል
  • አባገዳዎች
  • ሀደ ሲንቄዎች
  • የማህበረሰብ መሪዎች፤

 

  1. አማራ ክልል
  • የሀገር ሽማግሌዎች
  • የሴቶች ማህበራት
  • የገበሬ ህብረት ስራ ማህበራት በተጨማሪነት ተመልምለው ኮሚሽኑን እገዛን እንዲያደርጉ ተደርጓል፡፡

በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ ሁሉም ተባባሪ አካላት ወደ ስራ ከመግባታቸው በፊት ስልጠና በማዘጋጀት ተባባሪ አካላቱ  በተሳታፊ ልየታ ሂደት እና አተገባበር በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡

 

ይህንንም ተከትሎ የተጨመሩት አካላት ወደሚገኙባቸው የተለያዩ ወረዳዎች በመሄድ በኮሚሽኑ ከተለዩት የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊዎችን በመለየት ሂደቱ ተዓማኒ እንዲሆን አመርቂ ስራ ሰርተዋል፡፡

 

በእስከ ዛሬው ሂደት ኮሚሽኑ ከ6,000 በላይ ለሚሆኑ ተባባሪ አካላት ስልጠና በመስጠት የምክክር ሂደቱ በየማህበረሰቡ ወግና እና እሴቶች ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን ማድረግ የተቻለ ሲሆን የኮሚሽኑን ተዓማኒነትም ከፍ ለማድረግ ተችሏል፡፡

 

ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!